መሀል አዲስ አበባ ላይ ህጋዊ ፈቃድ አውጥተው ከ600 በላይ ወጣቶችን ያጭበረበሩ እና እያጭበረበሩ ያሉ የከተማችን ማፍያዎች!
መጋቢት 2014 ከ14 አመት በላይ የኖርኩባትን አዲስ አበባን ለቅቄ ወደ ቤተሰቦቼ ክፍለ ሀገር ተመለስኩ። ምክንያቴም ባለኝ የስራ ልምድ እና እውቀት ሰርቼ ራሴን መቀየርም ሆነ ማኖር ስለከበደኝ ነበር። እናም ወደ ክፍለሀገር ተመልሼ እንደነገሩ የግል ስራ ጀምሬ ሁለት ዓመት አካባቢ ሰራሁ። ግን እዚህም አንድም በሰላም እጦቱ(በጦርነቱ) ሲቀጥል ከአካባቢው ሰው(ምንም እንኳን የተወለድኩበት አካባቢ ቢሆንም) ጋር ለመግባባት በመቸገሬ ነገሮች እንዳስብኩት ቀላል አልሆኑልኝም። ከአዲስ አበባ አንፃር ሳየው እዚህ ቢያንስ ስለቤት ኪራይ እናም ስለአስቤዛ ባላስብም ግን ስለነገዬ አለማሰብ አልቻልኩም ነበር እናም ዝም ብሎ መኖር ሲደክመኝ ከአገር ስለመውጣት ማሰብ ጀመርኩ።

ወጥቼ አምስት ስድስት ዓመት ሰርቼ እመለስ እናም እዚህ የተሻለ ኑሮ እኖራለሁ ቢያንስ በምን እኖራለሁ? የሚለውን ጥያቄ በሚገባ እመልሳለሁ በሚል ወደ ውጭ የሚልኩ ኤጀንሲዎችን ማፈላለግ ጀመርኩ። መጀመሪያም ለክትትል እንዲመቸኝ ያለሁበት አካባቢ ነበር ያፈላለኩት ነገር ግን በሰዓቱ እዚህ ያገኘኋቸው ኤጀንሲዎች ላይ እምነት ማሳደር አልቻልኩም ነበር። ምክንያቱም አብዛኞቹ አንድ ጠባብ ክፍል ቢሮ ተከራይተው በዛ ላይ አንድ ሰራተኛ ብቻ ይዘው ነው እየሰሩ የነበረው።እናም ነገ ስመለስ ቢሮው ተዘግቶ ባገኘውስ? በሚል ፍራቻ የዚህን ሀሳብ ዘግቼ ወደ አዲስ አበባ ተመለስኩ። ከዚህ ከመነሳቴ በፊት “የሆነ አሪፍ አማካሪ ድርጅት አለ አሪፍ ነው የድርጅቱ ባለቤት በጣም ሰፊ ኔትወርክ ያላት ናት ። የእነ…..እህትም እዚያው ነው የምትሰራው” ብለው ድርጅቱ ውስጥ የምትሰራ(ሴልስ) እናም የምኖርበት ከተማ ልጅ ስልክ ሰጥተውኝ ነበር እናም ደውዬ ሳናግራት “ብዙ አማራጮች አሉን ቢሮ መጥተህ አናግረን” አለችኝ። ይሄን እንደ አንድ እናም የተሻለ አማራጭ ይዤ ወደ አዲስ አበባ ተመለስኩ። በጊዜው አራት ኪሎ አምባሳደር ህንፃ ወደነበረው ቢሯቸው ስገባም በዓይኔ ያየሁት ነገር ከሴልሶች በላይ የማሳመን ብቃት ነበርው። የቢሯቸውን የውስጥ ዲዛይን ውበት እናም ስፋት ሳይ መቼም የሚዘጋ(ስጋቴ ዘግተው ይጠፋሉ የሚል ስለነበር) መስሎ አልተሰማኝም ነበር። በዛ ላይ የጠቅላይ ሚንስተር ዶ/ር አብይ አህመድን እና የቀድሞ ፕሬዝዳንት የነበሩትን ሳህለወርቅ ዘውዴን ፎቶ በትልልቅ ፍሬም አሰርተው ፊት ለፊት ሰቅለው ነበር ይሄም ለእነሱ አንድ ማሳመኛ መንገድ ነበር። ተሳክቶላቸዋልም። በድርጅቱ ስም አንዳንድ መረጃ ድህረ ገፅ ላይ ስፈልግም ትልልቅ እናም ተፅዕኖ ፈጣሪ አርቲስቶች ሲያስተዋውቁት አየሁ እናም የበለጠ እምነት አደረብኝ። ከምንም በላይ ይሄን ድርጅት እንድመርጥ ያደረገኝ ደግሞ በሰዓቱ በአንዴ ሙሉ ክፍያ ከፍዬ የምሄድበት አቅሙ ስላልነበረኝ እናም እነሱ ጋር በዱቤ በመሆኑ ነበር። “ከ10% እስከ 25% ቅድመ ክፍያ ብቻ ከፍለው ቀሪውን የሚሄዱበት አገር እየሰሩ ይከፍላሉ” ስለተባልኩ በ25% vip አማራጭ 167,750(አንድ መቶ ስልሳ ሰባት ሺ ሰባት መቶ አምሳ) ብር ከፍዬ ውል የተዋዋልኩት። ከዛ በኋላ “የስራ ፍቃድ መጥቶላችኋል እናም ለጊዜው ገንዘብ ስላጠረኝ ነው ፕሮሰሳችሁ ቶሎ እንዲያልቅላችሁ…..” እያለች በተለያዬ ጊዜ ከመጀመሪያ ውላችን ውጭ ብዙ ገንዘብ አስከፍላናለች። መክፈል ያልቻለ refound ሞልቶ ገንዙቡ ተመላሽ እንዲሆለት መጠበቅ ጀመረ። ገንዘባቸውን ባያገኙም ቅሉ። በብድርም ሆነ ንብረት ሽጠን መክፈል የቻልን ደግሞ የጠየቀችንን ገንዘብ በሙሉ ብንከፍልም መጨረሻ ላይ “አልተሳካም” አለችን። እኔ በግሌ በaim ultra education consultancy 586,000(አምስት መቶ ሰማንያ ስድስት ሺ) ብር ከፍያለሁ።

ምንም ቪዛ ባልተመታበት ሁኔታ የአየር ቲኬት፣ የኮቴ እናም የትራቭል ኢንሹራንስ በሙሉ አስከፍላናለች። ለአንድ ዓመት ያክል ፕሮሰሱን ስከታተል የነበረው ደግሞ ከክፍለ ሀገር በፕሌን(በጦርነት ምክንያት የየብስ ትራንስፖርት ዝግ ስለነበር) እየተመላለስኩ ነበር በዚህም ለፕሌን እናም ለአልጋ ከ120,000(ከአንድ መቶ ሀያ ሺ)ብር በላይ አውጥቻለሁ።ሌሎች ከ600-1000 የሚደርሱ(ትክክለኛ ቁጥሩን ማወቅ ያልቻልኩ) ተበዳዬችም aim ultraን ጨምሮ በተመሳሳይ ግለሰቦች በሚዘወሩ እናም በተለያዩ ድርጅቶች ከ40,000(አርባ ሺ) እስከ 800,000(ስምንት መቶ ሺ) እናም ከዛ በላይ ተበልተዋል። በዚህ የማጭበርበር ተግባር ምክንያት የሰው ህይወት ጠፍቷል፣ ትዳር ፈርሷል፣ ቤተሰብ ተበትኗል የብዙ ወጣቶች ህይወት ሲዖል ሁኗል! እኔ ፕሮሰሱን ስጀምር ቢያንስ 200,000 ብሩ የራሴ ገንዘብ ነበር። ሌላው በተለያዬ መንገድ የተቀበልኩት የቤተሰብ፣ የጓደኛ ፣ብሎም የእቁብ ብር ስለነበር ይሄንን መመለስ ባለመቻሌም ከቤት የመውጣት ሞራል አጣሁ! ስለእውነት አሁን ላይ ሙሉ ገንዘቤን ብትመልስልኝ እንኳን የማልሸፍነው እዳ ውስጥ ገብቻለሁ። ብዙ ነገር አጥቻለሁ። ከቤተሰብ ጋር ተቆራርጫለሁ! ገንዘብ በሰጡኝ ሰዎች ፊት አንገቴን ለመድፋት ተገድጃለሁ! “ከአልጋ ላይም ለመነሳት ተስፋ ያስፈልጋል” እንዲል አዳም ከአልጋ ላይ የምነሳበት ሞራል እያጣሁ ብዙ ቀኖችን አልጋዬ ላይ እያሳለፍኩ አለሁ! ጉዳዩ ከተበላሸ ጀምሮ ንጋትን እየፈራሁ አለሁ! “በሰላም አሳድረኝ” ከሚለው በተቃራኒ እየፀለይኩ ወደ መኝታዬ መግባት ከጀመርኩ ቆየሁ! ሁሉም ነገር ያደክማል! ከማስታወሻዬ ውጭ ለቅርብ ቤተሰቤ እንኳን አውርቼው የማላውቀውን ችግሬን እናም መከፋቴን ሁሉ በዝርዝር ነግሬያት ነበር እንኳንስ አዝና ገንዘቤን ልትመልስልኝ ለመልዕክቴ እንኳን መልስ አልሰጠችኝም። ብቸኛ መፅናኛዬ “እንኳንም እሷን አልሆንኩ ነው”! ለሚያስብ እናም ከህሊናው ላልራቀ ሰው ከመበደል መበደል ይቀላልና! እሷ ግን እንደ ሰው ሀዘን እና ደስታ የሚፈራረቅባት ስለመሆኗም እጠራጠራለሁ! በፈጣሪ በሚያምን ሰው በዚህ ልክ መበደሌ(በደሉ የእኔ ብቻ ባይሆንም) ደግሞ የበለጠ ግራ አጋብቶኛል። “ለስራችን እንደስራችን ዋጋ የሚከፍል አምላክ አለ” ብሎ ከሚያምን ሰው በዚህ ልክ ጭካኔ? ብዙ ነገር እየገባኝ አይደለም። እናም ካልተሳካ ገንዘባችንን መልሽ ስንላትም “ገንዘቡን ሰርቼበታለሁ አሁን ላይ ካሽ የለኝም” ነበር መልሷ። እውነቱ ከእኛ በሰበሰቡት ገንዘብ ሌላ ስራ እየሰሩበት እንጂ ምንም ፕሮሰስ እያደረጉ እንዳልነበር ነው መጨረሻ ላይ የተረዳነው። እኔ የተጭበረበርኩት AIM Ultra Education Consultancy ነው። ይሄ ድርጅት ግን ከአንድ ብዙ አልጋ ካለው ሆቴል ውስጥ አንዱ ክፍል ብቻ ነው። ተመሳሳይ ሰዎች የሚዘውሯቸው ብዙ ድርጅቶች አሉ። ዋናዋ ዘዋሪ ቤተልሄም ታደሰ ይማም ትባላለች። ሴትዮዋን ተከታትሎ ለመያዝም ሆነ ለማስያዝ ከባድ ያደረገው ደግሞ በተለያዩ የቤተሰብ አባል ነው ፍቃድ የምታወጣው እናም ድርጅቶችን የምትከፍተው ። መኖሪያ አድራሻም ስለምትቀያይር ማግኘት አልቻልንም። አንድ ድርጅት ትከፍት እናም መዝረፍ ያለባትን ዘራርፋ እሱን ትዘጋ እና በሌላ ሰው ስም በአዲስ ፈቃድ በአዲስ ስም ትመለሳለች እንዲህ እያለች ትቀጥላለች ….. በእርግጠኝነት ይቺ ሴትዮ በጊዜ በህግ ቁጥጥር ውስጥ ካልዋለች ገና ብዙ ግፍ እናም ማጭበርበሮች እንሰማለን! ብዙ ጊዜ የእሷ ድርጅት መሆኑ የሚረጋገጠው ነገሩ ከተበላሸ በሗላ ነው። ሲበዛ በብዙ ሌብነት የተካነች አደገኛ ሴት ናት። ነገሩን ስላቅ የሚያደርገው ደግሞ ምርጥ ስራ ፈጣሪ ሴት ተብላ መሸለሟ እናም በዚሁ ዘርፍ አገራችንን ወክላ ደቡብ አፍሪካ ድረስ ሂዳ መሳተፏ ነው። ሌላው ደግሞ በጣም ያስገረመኝ እናም ያሳዘነኝ ነገር እኔ በተጭበረበርኩበት ድርጅት ባይሆንም ከታች ከጠቀስኳቸው ድርጅቶች በአንዱ የተጭበረበሩ ተበዳዮች በሜን ስትሪም ሆነ በፖድካስት ሚድያ ቀርበው አቤት ብለው እንኳን ምንም እርምጃ አለመወሰዱ ነው። የብዙ ጊዜ ዛቻዋም “ክስ አያዋጣችሁም ትጎዳላችሁ” ነበር። እየሆነ ያለውም ይሄው የእሷ ቃል ይመስላል። በርግጥ እኔ በግሌ ምንም የቀረኝ ነገር አልነበረም እናም ወደ አዲስ አበባ መምጣትም ሆነ ክስ መመስረት የምችልበት አቅሙ ስለሌለኝ ለጊዜው እየደወልኩ ፣በመልዕክት እናም በቮይስ ከመለመን ውጭ እስካሁን የሞከርኩትም ሆነ ያደረግኩት ነገር የለም። እሱ የሚኖሩ አብዛኞቹ ተበዳዬች ግን በብዙ እየደከሙ እንደሆነ አውቃለሁ እስካሁን መፍትሄ ባያገኙም። ከእነዚህ ድርጅቶች ውስጥም እኔ በግሌ የደረስኩባቸው የድርጅት ስሞች፦
1,ኢትዮ ኤርስ ንግድና ኢንቨስትመንት ሃ/የተ/የግ/ማ
2,ሩቢ ቪዛ ኮንሰልታንሲ ሶሉሽን
3,ኤ አይ ኤም አልትራ ኢዱኬሽን ኮንሰልታንሲ
4,ካባ ሆልዲንግ ካምፓኒ
5,የሎው ካርድ ኮንሰልታንሲ
6,ፔስኮ ፔስት ሶሉሽን
7,ጆፕሊንክ ማንፓወር ሶሉሽን……
ከሌሎች ተበዳዮች ባገኘሁት መረጃ ድርጅቶች ከ12 በላይ እንደሆኑ ነው የሰማሁት(ያረጋገጥኩት ባይሆንም)
እነዚህን ድርጅቶች በሚድያ የሚያስተዋውቁላቸው ደግሞ በህዝብ ዘንድ ተፅዕኖ ፈጣሪ እና ተሰሚነት ያላቸው አርቲስቶች ናቸው። ከእነዚህም ውስጥ
1, አርቲስት? ዳናይት መክብብ
2,አርቲስት ሩታ መንግስተኣብ
3,አርቲስት አምለሰት ሙጬ
4,አርቲስት ሙሉዓለም ታደሰ
5,ቲክታከር ዩቲ ናስ
5,ቲክታከር ፊዮና….
እነዚህን ድርጅቶች የሚዘውሩ ግለሰቦች ደግሞ፦
2,ገሊላ በለጠ ሳህሉ
3,በለጠ ሳህሉ
4,አቤል ተስፋዬ አሻግሬ
5,ሩት መኮንን
6, ዳዊት በለጠ
7,እዮሲያስ ታደሰ ይማም እናም ሌሎች
በአጠቃላይ የቤተሰብ የማፍያ ኢምፓየር ነው እየገነቡ ያሉት።
እናም በሚመለከተው አካል ተጣርቶ ተገቢውን እርምጃ እንዲወሰድ እጠይቃለሁ! ለቀጣይም መሰል ማጭበርበሮች እንዳይፈፀሙ እኛም ተበዳዬች ፍትህ እንድናገኝ ማንኛውም ጋዜጠኛ፣ አክቲቪስት እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች እባካችሁን በምትችሉት ሁሉ ይሄን መረጃ ይመለከተዋል ለምትሉት የመንግስት አካልም ሆነ ተቋም አድርሱልን! ይሄ የግለሰብ ችግር አይደለም የብዙ ገንዘባቸውን ፣ተስፋቸውን እናም እድሜያቸውን ሳይቀር መሀል አዲስ አበባ ላይ ህጋዊ ፈቃድ ባላቸው ህገ ወጥ ሰዎች የተጭበረበሩ ወጣቶች ድምፅ ነው!
ፎቶዋን አስተያየት መስጫው ላይ አስቀምጣለሁ የሰው በደል የሚሰማችሁ እናም የምትኖርበትን አካባቢ የምታውቁ በውስጥ መስመር አሳውቁኝ ( ፀሐፊ Lela Sew )