🔴 “ የአማራ ክልል ምሁራንና ሊህቃን በሰፊው እስር ቤት ነው ያሉት። አንድ ህዝብ ሊህቃን ታስሮበት ሊሳተፍ አይችልም ” – ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር)
➡️ “ ጫካ ውስጥ ያሉ ሰዎች አጀንዳ አልመጣም ብዬ አላስብም ” – ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር)
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሦስት ዓመታት ሪፓርት ለፓርላማ ማቅረቡ፣ የካቲት 14 ቀን 2017 ዓ/ም ሦስት አመቱን የሚደፍነው የኮሚሽኑ የሥራ ጊዜ በቋሚ ኮሚቴው ለአንድ አመት መራዘሙ ታውቋል።

ኮሚሽኑ በሪፓርቱ፣ በ10 ክልሎችና በሁለት ከተማ አስተዳደሮች የምክክር፣ የአጀንዳ ልየታ እና ለሀገራዊ ምክክር የሚሳተፉ ተወካዮች የማስመረጥ ተግባራትን እንዳጠናቀቀ አመልክቷል።
በአማራ ክልል ያለው ሥራ መቀጠሉን፣ የትግራይ ክልል ገና መሆኑም ተመላክቷል።
ሪፓርቱ በቀረበበት ወቅት የፓርላማ አባት ያነሷቸው ጥያቄዎች ምንድን ናቸው ?
የኮሚሽኑ ሪፓርት ከቀረበ በኋላ አብዛኛዎቹ የፓርላማ አባላት በተለይ የጸጥታ ችግር ያሉባቸው አካባቢዎች ለምክክሩ የገጣማቸውን የተሳትፎ ውጥንቅጥ የሚመለከቱ ጥቄዎችን ሰንዝረዋል።
አንድ የፓርላማ አባል፣ የጸጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ማኅበረሰቡ በንቃት ነው የተሳተፈው? ለሀገር እንቅፋት የሆኑ ነገሮችን ለማስቀረት ኮሚሽኑ ምን እየሰራ ነው? የሚሉ ጥያቄዎችን አቅርበዋል።
ሌላኛው የፓርላማ አባል ደግሞ፣ ፓርቲዎች ከምክክሩ የወጡበት ምክንያት ምንድን ነው? አጀንዳቸውን አሁንስ በምን መልኩ ነው የሚሰጡት? በማለት ጠይቀዋል።
የታጠቁ ኃይሎችና አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በምክክሩ እንዳልተሳተፉ ሲናገሩ የተደመጡት ሌላኛው የፓርላማ አባል፣ ወደ ፊት ኮሚሽኑ በዚሁ ጉዳይ ምን ለመስራት እንዳሰበ ማብራሪያ ጠይቀዋል።
ለጥያቄዎቹ ምላሽ የሰጠው ኮሚሽኑ በበኩሉ፣ የጸጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎችም የህዝቡ ተሳትፎ ጥሩ እንደነበር፣ ፓርቲዎችም ሆኑ ታጣቂዎች አሁንም አጀንዳቸውን ካቀረቡ በሩ ክፍት መሆኑን ገልጿል።
የፓርላማ አባሉ ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) ምን ጠየቁ?
ጠንከር ያሉ ሀሳቦችን በማቅረብ የሚታወቁት የፓርላማ አባሉ ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር)፣ “የአማራ ክልል ምሁራንና ሊህቃን በሰፊው እስር ቤት ነው ያሉት። አንድ ህዝብ ሊህቃን ታስሮበት ሊሳተፍ አይችልም” ሲሉ ተችተዋል።
በትጥቅ ትግል ላይ ያሉ አካላት አጀንዳቸውን እንዳላቀረቡ፣ የአካታትነት ችግር እንዳለ ገልጸው፣ “ይህ ባልተካሄደበት ሁኔታ ምን አይነት ምክክር ማድረግ ይቻላል?” ሲሉም ጠይቀዋል።
በአማራም ሆነ ኦሮሚያ ክልሎች ባለው ጦርነት ኮሚሽኑ የተኩስ አቁም ጥሪ ማድረግ እንደሚገባው ገልጸው፣ “ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የቁርጠኝነት ችግር እንዳለ አያለሁ” ነው ያሉት።
እንዲሁም የጸጥታ ችግር ዜጎች ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው የመመካከር ደኅንነታቸው ላይ ችግር መፍጠሩንም የተናገሩ ሲሆን፣ “አማራ ክልል ህዝቡ ከፍተኛ ትራውማ ውስጥ ገብቷል። ከክልሉ ውጪ ያሉትም የማንነት ጥቃት ሰለባ ሆነዋል” ብለዋል።
ሥጋት ለሚያነሱ ሰዎች የተለያዩ ፍረጃዎች እየተሰጠ የሚኬደው ነገር ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ፣ ኮሚሽኑ በትጥቅ ትግል ያሉ አካላትን እንዲያካትት አስተያየት የሰጡ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ፣ መንግስትና በልጽግና አስቻይ ሁኔታ ፈጥሯል ወይ? ሲሉ ጠይቀዋል።
ለዚሁ ጥያቄ አጸፋ የሰጡት በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)፣ እነደሳለኝና አብን ፓርቲያቸው ምን አስተዋጽኦ አድርጓል? ሲሉ ጠይቀዋል።
የታጠቁ አካላት በምክክሩ ባለመሳተፋቸው ደሳለኝ (ዶ/ር) ባቀረቡት ትችት የተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) አጸፋ፣ “የታጠቁ ቡድኖችም ሁሉም አይደሉም ያልተሳተፉት” ሲሉ ተደምጠዋል።
የተሰወሱ የፋኖ ክንፎች ሁኔታም አንስተው፣ እነ ጃል ሰኒ ደግሞ በምክክሩ እንደተሳተፉ የገለጹ ሲሆን፣ “የቀሩት የሸኔ ክፋይ የተለዬ ሀሳብ አላቸው ብለን አናምንም” ብለዋል።
ተስፋዬ ዶ/ር)፣ ጉዳዩን እያጋጋልን ነው የቆየነው ወይስ ጉዳዩ ወደ መሀል እንዲመጣ አድርገን ለመፍትሄ እየሰራን? ሲሉም ፓርቲዎችን የተመለከተ ጥያቄ አቅርበዋል።
የሀገሪዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን ዓርዓያ (ፕ/ር) በበኩላቸው፣ ኮሚሽኑ በአማራ ክልል የተሳትፎ ልየታ እንዳደረገ፣ የቀሩት 8 ወረዳዎች ብቻ እንደሆኑ ምላሽ ሰጥተዋል።
በጫካ ስላሉ አካላት አጀንዳ አለመቅረብ በተመለከተ የቀረበውን ጥያቄ ሲመልሱም፣ “ጫካ ውስጥ ያሉ ሰዎች አጀንዳ አላመጡም ብዬ አላስብም” ብለው፣ በባሕር ዳር፣ ደብረ ብርሃን፣ ጎንደር ያሉ ክላስተሮች የሕዝቡን ችግር እንዳስረዷቸው ተናግረዋል።