ጅቡቲን ለበርካታ ዓመታት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ያገለገሉት መሐመድ ዓሊ ዩሱፍ ቀጣዩ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ኾነው ተመርጠዋል።
ኮሚሽኑን እንዲመሩ በሊቀመንበርነት የተመረጡት የጅቡቲው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ በአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ በተካሔደውና ብርቱ ፉክክር በታየበት፣ እንዲኹም እስከ ሰባተኛ ዙር ድረስ በዘለቀ ምርጫ ሁለት ሦስተኛ ድምጽ በማግኘት ነው።

ከሳምንት በፊት 60ኛ ዓመት የልደት በዓላቸውን ያከበሩት ዩሱፍ፣ የኬንያውን የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ እና የማዳጋስካር የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሪቻርድ ራንድሪያማንድራቶን በማሸነፍ ኮሚሽኑን በቀጣይ አራት ዓመታት እንዲመሩ ተመርጠዋል።
አዲሱ የኅብረቱ ተመራጭ ከአውሮፓውያን 2005 ጀምሮ የጅቡቲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል።
መሐመድ ዓሊ ዩሱፍ በአፍሪካ አህጉር ለረጅም ዓመታት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው የገለገሉም ናቸው።