18 የውጭ ኩባንያዎች ከኢትዮጵያ በመውጣታቸው 11 ሺሕ 500 ሠራተኞች ሥራ አጥ መሆናቸው ተሰማ

ኢትዮጵያ ከአሜሪካው የአፍሪካ የቀረጥ ነጻ ንግድ ዕድል (አጎዋ) መታገዷን ተከትሎ 18 የውጭ ኩባንያዎች ከአገሪቱ በመውጣታቸው 11 ሺሕ 500 ሠራተኞች ሥራ አጥ እንደኾኑ ብሄራዊ ባንክ በቅርቡ ያካሄደው አንድ ጥናት ጠቅሶ ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል።

በእገዳው ምክንያት ኢንዱስትሪ ፓርኮች በጠቅላላው 45 ሚሊዮን ዶላር ኪሳራ እንደደረሰባቸው ጥናቱ ማመልከቱን ዘገባው ጠቅሷል።

በእገዳው ከፍተኛ ኪሳራ ካጋጠማቸው መካከል፣ ከሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ 4 ሺሕ 321 ሠራተኞች፣ ከመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክ 2 ሺሕ 885 ሠራተኞች እንዲኹም ከቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ 1 ሺሕ 97 ሠራተኞች ሥራ አጥ መኾናቸውን ጥናቱ እንዳረጋገጠም ዘገባው አመልክቷል።

ከሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ብቻ ስምንት ኩባንያዎች ሙሉ በሙሉ የተዘጉ ሲኾን፣ ከቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ደሞ አምስት ኩባንያዎች ለቀው መውጣታቸውን ከጥናት ሰነዱ መመልከቱን ጋዜጣው ጠቅሷል።