ምርጫ ቦርድ ከአብይ አሕመድ ጋር የማደርገውን ውይይት እያደናቀፈ ነው ሲል ሕወሓት አማረረ

በደብረፅዮን ገ/ሚካኤል ( ዶ/ር) የሚመራው ህወሓት ምርጫ ቦርድ ላስተላለፈበት እግድ ምላሽ የሰጠ ሲሆን “ቦርዱ ከፌዴራል መንግስት ጋር የጀመርነውን ተከታታይ ውይይት ከማደናቀፍ እንዲቆጠብ እንጠይቃለን” ብሏል።

ከተመሰረተ ግማሽ ክፍለ ዘመን ያስቆጠረ አንጋፋ ፓርቲ መሆኑን የገለፀው ህወሓት  በመግለጫው ” ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካዋ የፕሪቶሪያ ከተማ የሰላም ውል ከተፈራረመ ጀምሮ ህጋዊነቴ የተመለሰ ነው ” ብሏል።

እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ህወሓት ከነሃሴ 3 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ህወሓትን በአዲስ ህግ እንደ አዲስ ፓርቲ ” መዝግቤዋለሁ ማለቱን ” አስገራሚ እና ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ፓርቲው አስታውቋል፡፡

“የምርጫ ቦርድ አካሄድ በመሰረቱ ተቀባይነት የሌለው ፤ ህግን መሰረት ያላደረገ ፣ትርጉም አልባ ውሳኔ ነው” ብሎታል።

“ህወሓት በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መሰረት ከኢትዮጵያ መንግስት እውቅና ተሰጥቶ የሰላም ውል የፈረመ ፓርቲ ነው ” ያለው ህወሓት ፤ ” ከኢፌዴሪ መንግስት ተከታታይ የፓለቲካ ውይይት በማካሄድ ላይ በመሆኑ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰላማዊ ውይይቱን ከማደናቀፍ እንዲቆጠብ ” ሲል አቋሙን ገልጿል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ህወሓት በልዩ ሁኔታ ከተመዘገበ ጊዜ አንሥቶ ባሉት 6 ወራት ውስጥ የቦርዱ ታዛቢዎች በተገኙበት ጠቅላላ ጉባዔ ማድረግ ይጠበቅበት የነበር  ቢሆንም ይህንን ባለማድረጉ ለሦስት ወር ከፖለቲካ እንቅስቃሴ እንዲታገድ ፤ በሦስት ወራት የዕግድ ጊዜ የዕርምት ዕርምጃ ሳይወስድ ቢቀር የፖርቲው ምዝገባ እንዲሠረዝ መወሰኑ ይታወሳል፡፡