ሕወሓቶች ለመስማማት ተስማምተዋል ተባለ

የሕወሓትን ኹለት አንጃዎች የሚመሩ አመራሮች ልዩነታቸውን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ባለፈው ጥር ወር የተፈራረሙትን የስነምግባር መመሪያ የስምምነቱ አመቻች የኃይማኖት አባቶች ዛሬ መቀሌ ውስጥ በሠጡት መግለጫ ይፋ አድርገዋል።

አመራሮቹ ለልዩነታቸው መፍቻ “ኃይልን ላለመጠቀም” በፊርማቸው እንዳረጋገጡ ከሰነዱ መመልከቱን ቢቢሲ ዘግቧል። የቡድኖቹ አመራሮች አንዳቸው በሌላኛቸው ላይ የበላይነትን ለማረጋገጥ ሲሉ ወደማንኛውም “የአመጽ ተግባር” ላለመግባትና “ማስፈራራት” እና “አመጽን” እንዲኹም “ተንኳሽ ንግግር” እና “የጥላቻ ቃላት” መጠቀምን ለመቃወም መስማማታቸው በሰነዱ ላይ እንደሠፈረም ዘገባው ጠቅሷል።

ይሄው ስምምነት ይፋ የሚደረገው የኹለቱ ቡድኖች አመራሮች በተገኙበት እንደኾነ በሰነዱ ላይ እንደተጠቀሰ ዘገባው የጠቀሰ ሲኾን፣ ዛሬ ሰነዱ ይፋ ሲደረግ ግን ተፈራራሚዎቹ ወገኖች አልተገኙም። የስነ ምግባር ሰነዱ እስካኹን ለምን ይፋ ሳይደረግ እንደቆየ የኃይማኖት አባቶች ማብራሪያ እንዳልሠጡም ዘገባው አመልክቷል። ሕወሓቶች ለመስማማት ተስማምተዋል።