የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ፣ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በመንግሥት ኃይሎችና ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች መካከል የሚካሄደው ግጭት፣ በአፋር ክልል ባንዳንድ ጊዜያዊ መጠለያዎች ለሚገኙ የርዕደ መሬት ተፈናቃዮች ሰብዓዊ ዕርዳታ ለማቅረብ በሚደረገው ጥረት ላይ እክል እንደፈጠረ አዲስ ባሠራጨው መረጃ አስታውቋል።
ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ያለው የጭነት ተሽከርካሪዎች እጥረትም፣ ለተፈናቃዮች ሰብዓዊ እርዳታ ለማጓጓዝ የሚደረገውን ጥረት እንዳስተጓጎለውና ተፈናቃዮች መተሃራ ከተማ ድረስ ሂደው እርዳታ ለመቀበል እስከ 18 ኪሎ ሜትር ድረስ በእግር መጓዝ ግዴታ እንደሆነባቸው ቢሮው ጠቅሷል።
በአፋር ክልል ተደጋጋሚ ርዕደ መሬት መከሰቱን ተከትሎ፣ 400 ሺሕ እንስሳት ወደ ሌላ አካባቢ እንደተጋዙም የቢሮው መረጃ አመልክቷል። ኾኖም ባካባቢው አስተማማኝ የግጦሽ እሳር እንደሌለና የረድኤት ድርጅቶች የእንስሳት መኖ እና መድሃኒት እያቀረቡ እንደኾነ ተገልጧል።
ቢሮው፣ በጊዜያዊ መጠለያዎች ለተጠለሉ ተፈናቃዮች የተሻሉ መጠለያዎችን መስራት፣ ተደራሽ ንጹህ የመጠጥ ውሃ እንዲሁም የተመጣጠነ ምግብና የጤና አገልግሎቶችን ማቅረብ እንደሚያስፈልግ ጠቁሟል።