አጥፊዎች ባልተጠየቁበት፣ የፖለቲካ እና የምርጫ ምህዳሩ ባልተከፈተበት ገለልተኛ፣ ፍትሃዊ፣ ነፃ፣ ዴሞክራሲያዊና በህዝቡ ዘንድ ተዓማኒ የሆነ ምርጫ እንዴት ማካሄድ ይቻላል ?

” አጥፊዎች ባልተጠየቁበት፣ የፖለቲካ እና የምርጫ ምህዳሩ ባልተከፈተበት ገለልተኛ፣ ፍትሃዊ፣ ነፃ፣ ዴሞክራሲያዊና በህዝቡ ዘንድ ተዓማኒ የሆነ ምርጫ እንዴት ማካሄድ ይቻላል ? ” – ፓርቲው

➡️ ” ቁጫ ምርጫ ክልል ላይ ምርጫ አስፈጻሚዎች፤ የምርጫ ክልል ጽ/ቤት ተደራጅተዋል። እንደማንኛውም ምርጫ ክልል ሥራችንን እየሰራን እንገኛለን ” – ቦርዱ

የቁጫ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቁዴፓ)፣ በምርጫ ክልሉ የፓለቲካ ምህዳሩ “ዝግ” እንደሆነ፣ “ድብደባ” እና “እስራት” እንዳልቆመ በመግለጽ፣ “ከድጥ ወደማጡ” የሆነው ሁኔታ በነጻነት ተንቀሳቅሶ ምርጫን ለመሳተፍ ፈተና እንደሆነበት ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጿል።

ፓርቲው በሰጠን ቃል፣ “በቁጫ ምርጫ ክልል ያለው የፖለቲካ እና የምርጫ ምህዳር ዝግ ነው” ብሏል።

እንዲሁም፣ “በተለመደ ሁኔታ ህዝቡ ይደበደባል፣ ይታሰራል፣ ይሳደዳል፣ ሁሉም የፓርቲያችን ጽሕፈት ቤቶች እንደወደሙ ናቸው” ብሎ፣ ወደምርጫ እየተገባ ያለው አጠቃላይ ሁኔታዎች “ከድጡ ወደማጡ” በሆኑበት ሁኔታ መሆኑን ገልጿል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይህን ለማረም ምን አይነት የመፍትሄ እርምጃ እንደወሰደ፣ “ችግሩን የፈጠሩ አካላት” በምርጫ አዋጁ ባልተጠየቁበት እና የፖለቲካና የምርጫ ምህዳሩ ባልተከፈተበት እንዴት ገለልተኛ፣ ፍትሃዊ፣ ነፃ እና በህዝቡ ዘንድ ተዓማኒ ምርጫ ማካሄድ እንደሚቻል ጥያቄ እንደፈጠረበት ገልጿል።

ፓርቲው፣ “አጥፊዎች ባልተጠየቁበት፣ የፖለቲካ እና የምርጫ ምህዳሩ ባልተከፈተበት ገለልተኛ፣ ፍትሐዊ፣ ነፃ፣ ዴሞክራሲያዊ እና በህዝቡ ዘንድ ተዓማኒ የሆነ ምርጫ እንዴት ማካሄድ ይቻላል?” ሲልም ጠይቋል።

የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ በሰጡት ምላሽ፣ “ቁጫ ምርጫ ክልል ላይ ምርጫ አስፈጻሚዎች፣ የምርጫ ክልል ጽ/ቤት ተደራጅተዋል። እንደማንኛውም ምርጫ ክልል ሥራችንን እየሰራን እንገኛለን” ብለዋል።

በተያያዘም፣ “ከምርጫም በፊት የፖለቲካ ፓርቲዎች ችግር ይደርስባቸዋል፤ ችግሩን ያቀርባሉ” ያሉት ሰብሳቢዋ፣ ቦርዱ ለዚህም ቅሬታ ያቀረበው ፓርቲ፣ የገዢው ፓርቲ እና የምርጫ ቦርድ ኃላፊዎች ያሉበት “ሦስትዮሽ ኮሚቴ” አቋቁሞ ችግር የተፈጠረበት ቦታ ድረስ በመሄድ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት ያደርጋል ብለዋል።

“ይሄ ሁሉ ተደርጎ ግን አሁንም ችግር አለ፤ ምርጫ ቦርድ ይህንን ያውቃል፤ ክትትል ያደርጋል” ያሉት ሰብሳቢዋ፣ ይህን ቦርዱ ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ደብዳቤ፣ ማሳሰቢያ እንደሚጽፍ ገልጸው፣ “አሁንም በቀጣይነት እየተሰራ ያለ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖለቲካ ምህዳሩ “ችግር ገጥሞታል” የሚል ቅሬታ እንደሚያቀርቡ ገልጸው፣ “ቦርዱ ከፓርቲዎች፣ ከገዢው ፓርቲ፣ ከጸጥታ አካላት ጋር ችግሩን ለመፍታት ጥረት እያደረገ ይገኛል” ብለዋል።