የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ውጥረት ከመቼውም በላይ በተካረረበት እንዲሁም በሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት የውጭ አገራት ጣልቃ ገብነት ዋነኛ መነጋገሪያ በሆነበት ወቅት የአፍሪካ ቀንድ እና የአረብ አገራት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ይፋዊ የሥራ ጉብኝቶች ተበራክተዋል።
ግብፅ እና ኢትዮጵያ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የተፋጠጡበት እንዲሁም ቀጣናዊ የኃይል አሰላለፍን የሚለውጡ ክስተቶች የበዙበት ወቅት እንደመሆኑ በአፍሪካ ቀንድ እና በአረብ አገራት የሚደረጉ ጉብኝቶች ከዲፕሎማሲያዊ ትስስር የዘለለ አንድምታ ሊኖራቸው ይችላል።
ለመሆኑ የየትኞቹ አገራት ባለሥልጣናት ወደ የትኞቹ አገራት ተጓዙ? በባለሥልጣናት መካከል ስለተደረጉ ውይይቶችስ ምን ተባለ?
ትናንት ረቡዕ ኢትዮጵያ የገቡት የሳዑዲ አረቢያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ልዑል ፋይሰል ቢን ፋርሐን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር በሁለትዮሽ እንዲሁም ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ መወያየታቸው ተገልጿል።
የውይይታቸው ዝርዝር ይዘት ይፋ ባይደረግም “በቁልፍ ዘርፎች ላይ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ትብብር ማጠናከር” እንዲሁም “የሁለቱም አገራት ፍላጎት በሆኑ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ መተባበር” ላይ ያተኮረ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው አስታውቀዋል።
የፎቶው ባለመብት, EBC
ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌድዮን ጢሞቴዎስ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ተጉዘው ከልዑል ፋይሰል ቢን ፋርሐን ጋር መወያየታቸው ይታወሳል።
ከሳዑዲው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ልዑል ፋይሰል ቢን ፋርሐን ጋር በተደረገው ውይይት “ሁለቱ አገራት የአፍሪካ ቀንድን ሰላም እና መረጋጋትን ለማስጠበቅ” በጋራ ለመሥራት እንደተስማሙ ተገልጿል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ ስለ ቀጣናዊ ደኅንነት እንዲሁም የፖለቲካ እና ምጣኔ ሃብት ትስስር መወያየታቸውን የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል። https://www.bbc.com/amharic/articles/c0e5nx2e9wqo