ኢትዮጵያ የሮይተርስ የዜና ወኪል ጋዜጠኞችን በሀገሪቱ የመሥራት መብት እንደነጠቀች የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘገበ። በመጪው ቅዳሜ እና እሁድ በአዲስ አበባ የሚካሔደውን 39ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ለሬውተርስ የተሰጠው ፈቃድ እንደተሰረዘ የዜና ወኪሉ ቃል አቀባይ በኢሜይል እንደገለጹ ዘገባው ይጠቁማል። ከዚህ በተጨማሪ መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ ሦስት የሬውተርስ ጋዜጠኞች በኢትዮጵያ የመዘገብ ፈቃድ እንዳልታደሰ ቃል አቀባዩ ገልጸዋል።
ሬውተርስ የውሳኔው ገፊ ምክንያቶች ምን እንደሆኑ ያለው ነገር የለም። ሁሉም ጋዜጠኞች ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ ሬውተርስ ስለ ኢትዮጵያ በሚሠራቸው ዘገባዎች የጀርባ አጥንት እንደነበሩ የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ገልጿል።
ሬውተርስ “ጉዳዩን እየገመገመ” እንደሚገኝ እና “ነጻ፣ ገለልተኛ እና አስተማማኝ በሆነ መንገድ” ስለ ኢትዮጵያ ዘገባዎች መሥራቱን እንደሚቀጥል አስታውቋል። የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት በጉዳዩ ላይ ለኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ያቀረበው ጥያቄ ምላሽ እንዳላገኘ በዘገባው ጠቅሷል። የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ባልደረባ ስለ ጉዳዩ መረጃ እንደሌላቸው መናገራቸውን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።
ሬውተርስ ከጥቂት ቀናት በፊት ለሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ታጣቂዎች በኢትዮጵያ ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ማሰልጠኛ መከፈቱን የሚዘግብ ሰፊ ሪፖርት አቅርቦ ነበር።
ከሁለት ሣምንታት ገደማ በፊት ዋዜማ ራዲዮ “በኢትዮጵያ ያለውን የሥራ ፈቃድ” ከተቆጣጣሪው የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በተሰጠው ትዕዛዝ እንደመለሰ ገልጾ ነበር።
ባለፈው ታኅሳስ ወር የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የዶይቼ ቬለ ሁለት ዘጋቢዎችን ፈቃድ በቋሚነት ሰርዟል። የቢቢሲ ዘጋቢዎች ፈቃድ እንዳልታደሰ የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።
ኢትዮጵያ በሪፖርተርስ ዊዝአውት ቦርደርስ የጎርጎሮሳዊው 2025 ዓመታዊ ሪፖርት በፕሬስ ነጻነት ከ180 ሀገራት 145ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።