የሕወሃት ሊቀመንበር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል፣ ሰሞኑን በአፍሪካ ኅብረት ጽሕፈት ቤት ጉባኤ የሚያካሂዱ የአባል አገራት መሪዎች የፕሪቶሪያው የግጭት ማቆም ስምምነት “ሙሉ በሙሉ”፣ “በአፋጣኝ” እና “በቅን መንፈስ” መተግበር እንዳለበት በይፋ እንዲያረጋግጡ ጠየቁ። ደብረጺዮን፣ መሪዎቹ በግጭት ማቆም ስምምነቱ ፈራሚ ወገኖች መካከል “ቅርጽ ያለው ፖለቲካዊ ንግግር” እንዲጀመር የሚያስችሉ ርምጃዎች እንዲወስዱ፤ የአፍሪካ ኅብረት የግጭት ማቆም ስምምነቱ መቆጣጠሪያ፣ መከታተያና ማረጋገጫ ሥርዓት ተግባራዊ እንዲሆንና እንዲጠናከር እንዲሁም የትግራይ ሕገመንግሥታዊ ሥርዓት ወደነበረበት እንዲመለስ፣ ተፈናቃዮች ደኅንነታቸውን በሚያስጠብቅ አኳኋን ወደ ቀያቸው እንዲመለሱና ለሲቪሎች ጥበቃ እንዲደረግ የሚያስችሉ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ ድጋፍ እንዲያደርጉም ለኅብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሞሃመድ የሱፍ እና ለኅብረቱ አባል አገራት መሪዎች ዛሬ በጻፉት ደብዳቤ ጠይቀዋል። አፍሪካ ኅብረት የግጭት ማቆም ስምምነቱን የመጠበቅ “የሕግ” እና “የሞራል” ሓላፊነት አለበት ያሉት ደብረጺዮን፣ በስምምነቱ አተገባበር ላይ የሚፈጠር “መዘግየት” እና “ብዥታ” ይበልጥ “አለመተማመን” እና “አለመረጋጋት” እየሠፋ እንዲሄድ ያደርጋል በማለት አስጠንቅቋል።