አቶ የሺዋስ አሰፋ ከአንድ ቀን እስር በኋላ ተፈቱ

የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ለቀጣዩ ምርጫ በዕጩነት ካዘጋጃቸው ተወዳዳሪዎች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ የሺዋስ አሰፋ ከአንድ ቀን እስር በኋላ ተፈቱ። አቶ የሺዋስ ዛሬ ረቡዕ የካቲት 4፤ 2018 ከቀኑ 10 ሰዓት ገደማ ተፈትተው በስልክ እንዳነጋገሯቸው የኢሕአፓ ፕሬዝዳንት አቶ አብርሃም ሃይማኖት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።May be an image of one or more people, eyeglasses and text

በተለያዩ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ለረዥም ጊዜ የፖለቲካ ተሳትፎ ያላቸው አቶ የሺዋስ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት፤ ትላንት ማክሰኞ ከቀኑ 8 ሰዓት ገደማ እንደነበር የኢሕአፓ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ይስሀቅ ወልዳይ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ገልጸዋል። አቶ የሺዋስ የተያዙት ከመኖሪያ ቤታቸው ውጭ ባለ ስፍራ መሆኑን ኃላፊው አስረድተዋል።

ፖሊስ ፖለቲከኛውን በቁጥጥር ስር ካዋለ በኋላ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዋና መስሪያ ቤት ወደሚገኘው ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ እንደወሰዳቸው ማረጋገጣቸውን ጉዳዩን ሲከታተሉ የቆዩት አቶ ይስሀቅ ተናግረዋል። ኢሕአፓ ዛሬ ረፋድ ላይ ባወጣው አጭር መግለጫ፤ በቅርቡ ፓርቲውን በተቀላቀሉት በአቶ የሺዋስ ላይ የተወሰደውን የእስር እርምጃ ተችቷል።

የአቶ የሺዋስ እስር በሰላማዊ መንገድ የፖለቲካ እንቅስቃሴ በሚያደርጉ ዜጎች ላይ “በመንግስት እየደረሰ ያለውን አፈና” ከሚያሳዩ “ተቆጥረው የማያልቁ ድርጊቶች” ውስጥ አንዱ እንደሆነ ፓርቲው በመግለጫው ላይ አስፍሯል። የእስር እርምጃው መጪው ምርጫ “ነጻ፣ ፍትሀዊ እና ዴሞክራሲያዊ ይሆናል” ከተባለው “በተቃራኒ እንደሚሆን አመላካች ነው” ሲል ኢህአፓ ኮንኗል።

ለአንድ ቀን በእስር ላይ የቆዩት አቶ የሺዋስ፤ ኢሕአፓ አባል የሆነበትን “ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት” የተሰኘ የፓርቲዎች ቅንጅት በመወከል በዘንድሮው ምርጫ ላይ ለመሳተፍ በዝግጅት ላይ ነበሩ። አቶ የሺዋስ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኝ የምርጫ ክልል ሊወዳደሩ መታጨታቸውን እና ለዚህም በምዝገባ ሂደት ላይ መሆናቸውን የኢሕአፓው ፕሬዝዳንት አቶ አብርሃም ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል።

🔴ዝርዝር ዘገባውን ለማንበብ ➡️ https://ethiopiainsider.com/2026/17394/