ኑ ጠላትን በጋራ ታግለን የአማራን ህዝብ ሕልውና እናረጋግጥ!
የካቲት 05 ቀን 2018 ዓ.ም
ከአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ የተላለፈ የምህረት አዋጅ
ሀ) መግቢያ:
አረመኔው የብልፅግና አገዛዝ የአማራን ህዝብ ህልውና አደጋ ላይ ለመጣል የጀመረውን ጦርነት ለማሳካት ይችል ዘንድ በርካታ አረመኔያዊ ተግባራትን ሲፈፅም መቆየቱ ይታወቃል።
የአማራን ህዝብ ያለ ልዩነት ለመፍጀት አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ እየተጠቀመ ያለው አገዛዝ የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ጂኦ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶችን በማገልገል በፈጠረው የማውደም አቅም ተማምኖ በከፈተው ጦርነት ራሱ እየተለበለበበት ይገኛል።
የአማራን ህዝብ ለማጥፋት ከሚጠቀምባቸው ስልቶች መካከል ነባሩን የብአዴን መዋቅር በመጠቀም ባሰባሰበው የምሊሻ እና የአድማ ብተና ኃይል ከፋኖ ጋር እንዲዋጋ እና ህዝባችን በሁለት ጎራ ተሰልፎ እንዲጠፋፋ የሞከረበት መንገድ አንደኛው ነው።
በአንድ ህዝብ መካከል እና በኢትዮጵያዊያን መካከል እንዲሁም ቀጠናዊ ጦርነቶችን በማስነሳት ለአፍሪካ ቀንድ የቀውስ ዘበኛ የሆነውን አገዛዝ በወንድማማችነት እና በጥበብ በማስወገድ የጋራ መንግስት መመስረት እንደሚገባን በተደጋጋሚ ጥሪወች ስናስተላልፍ የቆዬን መሆኑ ይታወቃል።
በተለይም ከሰሞኑ ደግሞ ጠላት በአንድ በኩል የህዝብ መገናኛ መስመሮችን በመዝጋት ንፁሃን ላይ ጭፍጨፋ እያደረገ በሌላ በኩል ደግሞ ብሔራዊ አጀንዳ ያለው እና ለሀገር ብሔራዊ ተልዕኮ የተሰለፈ በመምሰል የሚያደርገውን የማደናገሪያ ስልት በንቃት በመከታተል የፋኖ ሰራዊት በወሰዳቸው እርምጃወች ወራሪው የብልፅግና ኃይል ከፍተኛ ትርምስ ውስጥ ገብቷል።
የድርጅታችን የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ መወለድ ያስገኘው የአንድነት መንፈስ ለተገኙ ወታደራዊ ድሎች ቁልፍ ሚና ተጫውቷል። የድላችን ምስጢር ያለው አንድነታችን ላይ መሆኑም በተግባር ተረጋግጧል። ድርጅታዊ አንድነታችንን በጠበቀ መልኩ ከኢትዮጵያዊያን እና ከቀጠናው ኃይሎች ጋር የሚደረግ ትብብር አገዛዙን ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ ወሳኝ ሂደት መሆኑ ግልፅ ነው። ህዝባዊ ዓላማችንን የተጋራን ጋር በመርህ የምናደርገው ትብብር እና አንድነት የአረመኔውን አገዛዝ እድሜ ለማሳጠር ትልቅ ፋይዳ ያለው ጉዳይ ነው።
ይህንን ተከትሎ ባቀረብነው ወገናዊ ጥሪ በርካታ የአገዛዙ አገልጋይ የነበረ ምሊሻ፣ አድማ ብተና እና የመከላከያ ኃይል የወገንን ኃይል እየተቀላቀለ ይገኛል።
ስለሆነም ዛሬም አገዛዙን በማገልገል ላይ ለምትገኙ የምሊሻ፣ የአድማ ብተና፣ የመደበኛ ፖሊስ፣ መከላከያ እና በሌሎች የአገዛዙ ታጣቂ አደረጃጀቶች ውስጥ ላላችሁ ተመሳሳይ ጥሪወችን እናስተላልፋለን።
ይህንን ጥሪ ያስተላለፈው የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ ስራ አመራር በጉዳዩ ላይ በዝርዝር ተወያይቶ ጥሪዉን በመቀበል ወገናቸውን ለመካስ ለሚፈልጉ የአገዛዙ ሰራዊት አባላት እና የካድሬ መዋቅር የምህረት አዋጅ አውጇል።
ለ) የምህረት አዋጁ የተላለፈላቸው የአገዛዙ መዋቅር አካላት:-
፩) በየደረጃው የሚገኙ የብልፅግና አመራር አባላት
፪) ምሊሻ፣ ሰላም አስከባሪ እና በሌላም ስያሜ ብልፅግና ያደራጃቸው ታጣቂወች
፫) የክልል አድማ ብተና እና መደበኛ ፖሊስ አባላት
፬) በሀገር መከላከያ ሰራዊት ስም በየቀጠናው የተሰማሩ እግረኞች እና የአገዛዙ መኮንኖች
ሐ) የምህረት አዋጁን ማውጣት ያስፈለገበት ምክንያት
ሶስት ዓመታትን ሊደፍን ጥቂት ጊዜ በቀረው የጦርነት ሂደት በግልፅ መገንዘብ እንደሚቻለው የብልፅግና መዋቅር በአማራ ህዝብ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ድቀት ላይ ስልጣኑን ከማራዘም ያለፈ ለአማራ ህዝብ የሚጠቅም አንድም አጀንዳ የሌለው በመሆኑ የአማራ ህዝብ እንደ ህዝብ በተለያዬ ጎራ የተሰለፍን የአማራ ልጆችም እንደ የአንድ እናት ልጆች በመቀናጀት የህዝባችንን ህልዉና ማስጠበቅ ከእኛ የሚጠበቅ ተግባር ነው። በመሆኑም:-
፩) ለአማራ ህዝብ ሁለንተናዊ መብት እና ነፃነት እንጅ ለአብይ አህመድ ወንበር መፅናት የሚወድቅ የአማራ ወጣት መኖር ስለሌለበት፤
፪) ህዝባችንን በጅምላ ለሚጨፈጭፍ አገዛዝ በማገልገል የዘቀጠ ታሪክ ውስጥ ራስን ከማግኘት ይልቅ ለነፃነቱ የሚዋደቅን ኃይል በመቀላቀል ደማቅ ታሪክ መፃፍ ታሪክ የጣለብን ግዴታ በመሆኑ፤
፫) ህዝብን ታግሎ ያሸነፈ አገዛዝ እንደሌለው ሁሉ አብይ አህመድም የአማራን ህዝብ ማሸነፍ ስለማይችል እና በተሸናፊነት ለሚያጠናቅቀው ብልፅግና በመላላክ እና በራስ ወገን ላይ በመተኮስ የታሪክ፣ የህሊና እና የፍትህ ተጠያቂነትን ከማስተናገድ ለመዳን ሲባል፤
፬) አገዛዙን በጋራ ታግለን በማሸነፍ ለህዝባችን ሰላም ማምጣት የትውልዱ ግዴታ በመሆኑ፤
፭) እንዲሁም የምንታገለው ለአማራ ህዝብ ህልውናና መዳን እንደመሆኑ መጠን የፋኖ ትግልም የአማራ ህዝብ ትግል ስለሆነ በሁሉም ጎራ ላሉ አማራዊ ወንድሞች ጥሪ ማድረግ እና ማታገል የድርጅታችን ተልዕኮ በመሆኑ፤
ይህንን የምህረት አዋጅ በአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ ስራ አመራር ውሳኔ መሰረት ለህዝብ ይፋ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።
መ) የምህረት አዋጁ አተገባበር
፩) የምህረት አዋጁ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ካላይ በተራ ቁጥር “ለ” ስር የተዘረዘሩት የምሊሻ፣ አድማ ብተና፣ መከላከያ እና ሌሎች የታጠቁ የብልፅግና ኃይሎች እንዲሁም በየደረጃው ያሉ አመራሮች በየአካባቢያቸው ላለው የድርጅታችን መዋቅር እና ለዚህ ጉዳይ በተቋቋመው ግዜያዊ ግብረ ኃይል በአካል ቀርበው ሪፖርት ያደርጋሉ።
፪) ምህረት ጠይቀው ወገናቸውን ለመካስ የሚመጡ ግለሰቦች የአካል ደህንነት ዋስትና ይሰጣቸዋል። በተዘጋጀላቸው ማረፊያ የተሃድሶ ስልጠና እንዲወስዱ ይደረጋል።
፫) ለትግል አገልግሎት ከሚዉል የጦር መሳሪያን ጨምሮ ማንኛውም የምህረት ጠያቂወች ንብረት በባለቤቶች እጅ ይቆያል።
፬) ምህረት የተደረገላቸው ግለሰቦች ድርጅቱ ባዘጋጀው ፎርም መሠረት ለአማራ ህዝብ ነፃነት ሊሰሩ ካልተቻለም ከጠላት ወገን ላይሰለፉ ቃለ-መሃላ ይፈፅማሉ።
፭) አቅሙ እና ፍላጎቱ ያላቸው የምህረት ተጠቃሚወች የወገንን ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ መዋቅር ተቀላቅለው ለህልዉና ተጋድሎው የበኩላቸውን ድርሻ ይወጡ ዘንድ በሌላ ማናቸውም ለህዝብ ጠቃሚ በሚሆኑ ተልዕኮወች ላይ ይሰማሩ ዘንድ ድርጅቱ ሁኔታወችን ያመቻቻል።
፮) ይህ የምህረት አዋጅ ከዛሬ የካቲት 04 ቀ 2018 ዓ.ም ላሉት ተከታታይ 15(አስራ አምስት ቀናት) ብቻ ተፈፃሚ ይሆናል።
ሠ) የምህረት አዋጁን በማስፈፀም የሰራዊታችን እና የድርጅታችን አመራር ግዴታ
፩) የምህረት አዋጁን አፈፃፀም ለመከታተል በማዕከል የተቋቋመው ግብረ ኃይል የመመሪያዉን አተገባበር ይከታተላል፤ መረጃወችን ይሰጣል፤ መፍትሔ ያስቀምጣል።
፪) የድርጅቱ መዋቅር አመራር እና ሰራዊቱ ለምህረት ጠያቂወቹ የአካል ዋስትና መስጠትን ጨምሮ በእንክብካቤ በማስተናገድ በፍፁም ጨዋነት አዋጁን ይተገብራል።
፫)በአፈፃፀም ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮችን ወዲያውኑ ለግብረኃይይሉ ያሳውቃል፣ የተሰጠዉን የመፍትሔ አቅጣጫ ይተገብራል።
፬ በግል ቂም ቁርሾ ወይም በሌላ ግላዊ እና ቡድናዊ ፍላጎቶች ምክንያት ከዚህ አዋጅ በተቃረነ መንገድ በማንኛውም ምህረት ጠያቂ ላይ አካላዊ እና ስነ ልቦናዊ ጉዳት ማድረስ ወይም ንብረት መቀማት ፍፁም የተከለከለ ተግባር ነው።
፭) የዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌወችን እና መርሆወችን እንዲሁም ዓለም አቀፍ የጦር ህግጋትን የተከተለ አሰራር ይተገበራል።
፮) ይህንን አዋጅ ጥሶ የተገኘ ማንኛውም የድርጅቱ አመራር እና አባል ወይም ሌላ አካል ከባድ ቅጣት ይጠብቀዋል።
ረ) የሕዝቡ፣ የሀገር ሽማግሌወች እና የኃይማኖት አባቶች ሚና
በየቀጠናው ያለው ህዝብ፣ የሀገር ሽማግሌወች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ ምሁራን እና ሌሎች ተሰሚነት ያላቸው ግለሰቦች በጠላት የፀጥታ እና የፖለቲካ መዋቅር ውስጥ ያሉ ግለሰቦች በዚህ አዋጅ መሰረት አፈሙዛቸውን ወደ ዋናው ጠላት እንዲያዞሩ ካልሆነም ሰላማዊ ኑሯቸውን እንዲኖሩ እና የአማራው ኃይል ፍፁም ህብረት እንዲኖር የበኩላቸውን ገንቢ ሚና እንዲጫወቱ ይጠበቃል።
በመጨረሻም የአማራ ልጆች በጋራ ተባብረን ህዝባችንን ሊያጠፋ የተነሳውን ጠላት እናስወግድ ዘንድ አንድነት እና ህብረት ያስፈልገናል እና ወደ አማራ የምንተኩሰው ጥይት እንዳይኖር እና አንድ ጠላት ላይ ብቻ አነጣጥረን እናሸንፍ ዘንድ ኑ እንላለን።
የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ