የአብን የፓርላማ አባሉ ዶ/ር አበባው ደሳለው በመጪው ምርጫ ኢሕአፓን ወክለው ሊወዳደሩ ነው

የአብን የፓርላማ አባሉ ዶ/ር አበባው ደሳለው በመጪው ምርጫ ኢሕአፓን ወክለው ሊወዳደሩ ነው
በሰኔ 2013 ዓ.ም በተካሄደው ሀገር አቀፍ ምርጫ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄን ወክለው የፓርላማ አባል የሆኑት ዶ/ር አበባው ደሳለው፤ በመጪው ምርጫ ኢሕአፓን ወክለው ሊወዳደሩ ነው። የአብን የአዲስ አበባ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የነበሩት ዶ/ር ይህዓለም ታምሩም በተመሳሳይ መልኩ የፓርቲ ለውጥ አድርገው በመጪው ምርጫ እንደሚቀርቡ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ዛሬ ማክሰኞ የካቲት 3፤ 2018 ማምሻውን በበይነ መረብ በሰጠው መግለጫ ሁለቱ ቀድሞ የአብን አባላት ፓርቲውን መቀላቀላቸውን ይፋ አድርጓል። በበይነ መረብ የተካሄደውን መግለጫ ከሁለቱ የምርጫ ተወዳዳሪዎች ጋር በመሆን የሰጡት፤ የኢሕአፓ ዋና ጸሐፊ ሚስጥረስላሴ ታምራት ናቸው።
ሁለቱ የቀድሞ የአብን አባላት ለዘንድሮው ምርጫ በእጩነት የተመዘገቡት፤ ኢሕአፓ አባል በሆነበት “ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት” በተሰኘው የፓርቲዎች ቅንጅት በኩል መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ባለፈው መስከረም ወር የተመሰረተው ይህ የፓርቲዎች ቅንጅት፤ ከኢሕአፓ በተጨማሪ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ አንድ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ እና አማራ ግዮናዊ ንቅናቄ አባል የሆኑበት ነው።May be an image of one or more people and newsroom