ኤርትራ፣ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር የኤርትራ ሠራዊት በሰሜን ምሥራቅ ኢትዮጵያ ገፍቶ ይዟቸዋል ካላቸው መሬቶች ለቆ እንዲወጣና የኤርትራ መንግሥትም ለድርድር እንዲዘጋጅ ያቀረበውን ጥሪ አጣጣለች። የኤርትራ ማስታወቂያ ሚንስቴር፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ውንጀላ “ሐሰተኛ”፣ “የተፈበረከ” እና “በድምጸቱ”፣ “በይዘቱ” እና “ግቡ” አስገራሚ የሆነ ውንጀላ ነው በማለት ወቅሷል። ሚንስቴሩ፣ ውንጀላው ለሁለት ዓመታት የኢትዮጵያ መንግሥት በኤርትራ ላይ ሲያካሂደው የቆየው የጠበኛነት ዘመቻ አካል ነው በማለትም ተችቷል። ኤርትራ በጠብ ላይ አቀጣጣይ ነገር የመጨመር እና ሁኔታውን የማባባስ ፍላጎትም ሆነ ተነሳሽነት እንደሌላትም ሚንስቴሩ ገልጧል። የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ ለኤርትራው አቻቸው ኦስማን ሳለህ ባለፈው ሳምንት በላኩት ደብዳቤ፣ ሁለቱን አገሮች በሚያዋስኑት የሰሜን ምዕራብ ድንበሮች የኤርትራ ወታደሮች ከኢትዮጵያ አማጺ ቡድኖች ጋር “ጥምር ወታደራዊ እንቅስቃሴ” እያደረጉ ነው በማለት ጭምር ከሠው ነበር።