ከሽብር ክስ በነፃ የተሰናበቱት አዲስ የፍትሐ ብሔር ክስ ቀረበባቸው

የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ምክር ቤት አባሉ እና በቅርቡ ከገዥው ብልጽግና ፓርቲ ጋር የተዋሃደው የቀድሞው ተቃዋሚ የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አመራር የነበሩት ዮሐንስ ተሠማ፣ አዲስ የፍትሐ ብሔር ክስ ቀረበባቸው፡፡ የአሶሳ ከተማ አስተዳደር ፍትሕ መምሪያ በዮሃንስ ላይ አዲስ የመሠረተባቸው ክስ፣ ባለፈው ዓመት በ5 ዓመት ከ10 ወር እስር በተቀጡበት የከተማ መሬት ከሊዝ አዋጅ አግባብ ውጪ ከመያዝ ጋር የተያየዘ ነው፡፡ ዓቃቤ ሕግ ዮሐንስ በሕገወጥ የከተማ መሬት ይዞታ መንግሥትን 996 ሺህ ብር አሳጥተዋል በማለት ክስ የመሠረተ ሲኾን፣ የክሱ ዝርዝር ዛሬ የካቲት 2 ለተከሳሹ እንደደረሳቸው የተከሳሹ የቤተሰብ አባላት ለዋዜማ ተናግረዋል። ዮሐንስ ጠፋተኛ በተባሉበት የከተማ ሊዝ መሬት ለክልሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባቀረቡት ይግባኝ መሠረት ቅጣቱ ወደ አራት ዓመት ዝቅ እንደተደረገላቸው የገለጡት ቤተሰቦቻቸው፣ አሁንም ለፌደራል ከፍተኛ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ እንደጠየቁ ቤተሰቦቻቸው ነግረውናል። የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ ዓቃቤ ሕግ በዮሃንስ ላይ ለመሠረታቸው የሽብር ክሶች በቂ ማስረጃና ምስክር ማቅረብ አልቻለም በማለት ባለፈው ሳምንት በነጻ እንዳሠናበታቸው አይዘነጋም።