ጀኔራል ታደሠ ወረደ እና በዙሪያቸው ያሉ የሕወሃት አክራሪዎች እስካሉ ድረስ ትግራይ ከቀውስ አትወጣም ( ጌታቸው ረዳ)

የቀድሞው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ፣ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጀኔራል ታደሠ ወረደ እና በዙሪያቸው ያሉ የሕወሃት አክራሪዎች እስካሉ ድረስ ትግራይ ከቀውስ አትወጣም በማለት አስጠነቀቁ። ጌታቸው ፎርቹን ጋዜጣ ላይ ባወጡት ሃተታ፣ ጀኔራል ታደሠ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ምክትል ፕሬዝዳንት በነበሩበት ወቅት ሕወሃት ውስጥ የሚገኙ አክራሪዎችን ሲያባብሉና ጊዜያዊ አስተዳደሩን በተደጋጋሚ ቀውስ ውስጥ ሲከቱ ነበር በማለት ወቅሠዋል። ጌታቸው፣ ጀኔራል ታደሠ በእሳቸውና በአክራሪዎቹ መካከል አሸማጋይ መስለው በመቅረብ የፓርቲው ጥገኛ አድርገዋቸው እንደነበር በመጥቀስ፣ በኋላም ጀኔራሉ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት መኾናቸው በትግራይ ብዙ ጥፋት ማስከተሉን ገልጸዋል። ጀኔራል ታደሠ የክልሉን ኢንቨስትመንትና መሬት ጉዳዮች እንዲቆጣጠሩ የተሠጣቸውን ሃላፊነት ራሳቸውንና በዙሪያቸው ያሉ አካላትን ለማበልጸግ ተጠቅመውበታል ያሉት ጌታቸው፣ ጀኔራል ታደሠን ለፈጸሙት ሴራ እና ጥፋት ሁሉ አለመቅጣታቸው ስህተት እንደነበርም አውስተዋል።