ከአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ የተላለፈ ወቅታዊ መልዕክት

ከአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ የተላለፈ ወቅታዊ መልዕክት

አገዛዙ የአማራ ህዝብን አፍኖ ለመጨፍጨፍ የጀመረውን ማጥቃት በጽኑ ብሔራዊ አንድነት እንመክተዋለን !

የካቲት 03 ቀን 2018 ዓ.ም

የአብይ አህመደ አገዛዝ በአማራ ህዝብ ላይ ይፋዊ የዘር ማጥፋት ጦርነት ከጀመረ ሶስት ዓመታትን ሊደፍን ተቃርቧል። በእነኝህ ጊዜዎች ሁሉ የአማራ ህዝብ የታወጀበትን የዘር ማጥፋት ጦርነት በመመከት ህልውናውን ለማረጋገጥ የሚያደርገውን ትግል አጠናክሮ ቀጥሏል። ሆኖም በህዝብ ላይ ጦርነት ያወጀው አገዛዝ የገጠመውን ህዝባዊ ተጋድሎ ተረድቶ ጦርነት ከማቆም ይልቅ በእጁ የገቡትን የጥፋት መሳሪያወች ሁሉ ተጠቅሟል። በዓለም ታሪክ በማይታወቅ ሁኔታ በመንግስትነት ስም ቤተ መንግስት የከተመው አገዛዝ በአማራ ህዝብ ላይ ስትራቴጅክ ድሮኖችን በመጠቀም በሽህ የሚቆጠሩ ንፁሃንን ጨፍጭፏል። ቱርክን ጨምሮ አዳዲስ የጦር መሳሪያ አምራች ሀገራት ያመረቷቸውን ድሮኖች በአማራ ህዝብ ላይ ይሞክሩ ዘንድ አብይ አህመድ እና አገዛዙ በጭካኔ ፈፅመውታል።

አገዛዙ የባህረ ሰላጤው ኃይሎችን ፖለቲካዊ ፍጥጫ ጎትቶ ሀገር ውስጥ በማስገባት በተላላኪነት በሚያገኘው ወታደራዊ እና የመረጃ ድጋፍ ተጠቅሞ በህዝባችን ላይ ያወጀውን የዘር ማጥፋት ጦርነት አጠናክሮ ቀጥሏል። በዚህም አገዛዙ ጌቶቹ በቀጠናው ላቀዱት የተልዕኮ ጦርነት አማራን ማጥፋትን እንደ መንደርደሪያ ቆጥሮ፣ በድጋፍ ያገኘውን የማጥፋት አቅም በሙሉ ተጠቅሞ በሸዋ፣ በወሎ፣ በጎጃም እና በጎንደር የተለያዩ ቀጠናወች የስልክ እና የኢንተርኔት መሰረተ ልማቶችን በመዝጋት የተጠናክረ ጭፍጨፋ እያደረገ ይገኛል።

በተለይም በጥር ወር የመጨረሻ ሳምንት በሸዋ የአገዛዙ ሰራዊት የተለያዩ አሀዶች የኦሮምያ ልዩ ዞን ታጣቂወችን በመጨመር በሌሎች አካባቢወች ደግሞ በመደበኛወቹ እዞች እና የአየር ወለድ እና ኮማንዶ አሃዶቹ የከፈተው ማጥቃት በህዝባዊው የአፋብን ሰራዊት በሚገባ እየተመከተ ይገኛል።

ከየካቲት 01 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በሰራዊታችን በተደረገው የመልሶ ማጥቃት እርምጃ በጎንደር ቀጠና በርካታ ጀብዱወች ተፈፅመዋል። በተለይም በደቡብ እና ማዕከላዊ ጎንደር የወረዳ ዋና ከተሞችን ጨምሮ በርካታ ይዞታወችን ከጠላት መንጠቅ ተችሏል። በዚህ አስደናቂ ተጋድሎ በሺወች የሚቆጠሩ የአገዛዙ ሰራዊት በምርኮኛነት እና በፈቃዳቸው የወገንን ኃይል መቀላቀል ችለዋል። የወገን ሰራዊት በርካታ የቡድን እና የነፍስ ወከፍ መሳሪያወች፣ ተተኳሾች እና ሌሎች ወታደራዊ ቁሳቁሶችንም መማረክ ችሏል።

በጎጃም ቀጠና አገዛዙ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰራዊት ያሰማራበት የጃዊ አካባቢ ሰራዊታችን በወሰደው የመልሶ ማጥቃት እርምጃ አገዛዙን ሰራዊት ጨምሮ በርከት ያለ የቡድን እና የነፍስ ወከፍ መሳሪያ ከነተተኳሹ ከጠላት እጅ ተማርኳል።

እድል ባገኘ ግዜ ሁሉ ህዝብ ለመጨፍጨፍ የማያመነታዉን አረመኔ ሰራዊት በምርኮ፣ በድምሰሳ እና በማንኛውም መንገድ ከስምሪት ውጭ ማድረግ እና በእያለበት ውጦ ማስቀረት ሰራዊታችን በሚገባ እየፈጸመው ያለ ተልዕኮ ነው። ለዚህም የዘር ማጥፋት ጦርነቱ ዒላማ የተደረገው መላው የአማራ ህዝብ ለሰራዊታችን ያሳዬው ቁርጠኛ ደጀንነት በግምባር ለተገኙት ድሎች አስተዋጽኦው ትልቅ ነው። ሰራዊታችን በተቆጣጠራቸው የተለያዩ ከተሞች ህዝቡ ለሰራዊታችን የሞቀ አቀባበል ከማድረግ ባሻገር በመልሶ ማጥቃቱ የተገኙ ድሎች እንዲቀጥሉ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።

እነኝህ ድሎች ይገኙ ዘንድ የድርጅታችን የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ መወለድ በሰራዊታችን እና በህዝቡ ዘንድ የፈጠረው አዲስ ወኔ እና መነቃቃት ለድሎቹ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው። በተጨማሪም የአደረጃጀት አንድነቱ አቅማቸንን አቀናጅተን በውጤታማ የሀይል አጠቃቀም በጠላት ላይ ወሳኝ ምት ለማሳረፍ በማስቻሉ ብሔራዊ አንድነቱ የዘር ማጥፋቱን ጦርነት ለመመከት ያለው እምቅ አቅም የታየበት ነው። ህዝብን ታግሎ ያሸነፈ አገዛዝ በታሪክ እንደሌለው ሁሉ የህዝብ ልጅ የሆነው ሰራዊታችን፣ የአማራን ህዝብ ሙሉ ድጋፍ ያገኘው ድርጅታችን አፋብን የብሔራዊ አንድነትን አቅም ተጠቅሞ በተሰላ እና በተጠናከረ ሁኔታ የህልውና ተጋድሎውን ለድል እንዲበቃ ሁሉም አመራሮች እና አባላት የተሰጣቸውን ሀላፊነት ለመወጣት በትጋት እየሰሩ ይገኛሉ።

ሰራዊታችን እንደከዚህ በፊቱ ሁሉ በተቆጣጠራቸው ቦታወች ሰላም እና ፀጥታን በማስከበር እና በወታደራዊ ጨዋናት ጠላትን ብቻ የለዩ ዒላማወች ላይ በማተኮር ተገቢውን ጥንቃቄ እያደረገ እንደሚቀጥል ለመላው የአማራ ህዝብ፣ ለኢትዮጵያዊያን እና ለዓለም አቀፋ ማህበረሰብ እናሳውቃለን።

በመጨረሻም በመልሶ ማጥቃት የተመከተው የአገዛዙ የጥፋት እጅ ዳግም በማያንሰራራበት ሁኔታ ይመታ ዘንድ መላው ሰራዊታችን እና ህዝባችን የሚያደርገውን ርብርብ አጠናክሮ እንዲቀጥል እናሳስባለን።