ስማቸውን ሳንጠቅስ አስተያየታቸውን ብቻ እንድናስተናግድ የጠየቁን አንድ የሰላምና ደኅንነት ባለሙያ “በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሻከረ ነው” በሚለው ድምዳሜ ነው ምልከታቸውን የጀመሩት። “መደበኛ የሚባለው” የኢትዮጵያ እና የኤርትራግንኙነት “በጣም ተዳክሞ” ያለበት ወቅት ስለሆነ የደብዳቤው መውጣት “እንዳስገረማቸው” አልሸሸጉም።
ደብዳቤው በበጎ ከታየ ያሉ ሰላማዊ መንገድ እና አማራጮችን የመጠቀም “ኹኔታ ይመስላል” ብለዋል። የደብዳቤው ይዘት “ሊመጣ የሚችል” ችግርን “የሚጠቁም” ጭምር ነው – የሰላምና ደኅንነት ባለሙያው
ይህ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ደብዳቤ የወጣው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በባለፈው ሳምንት የፓርላማ ማብራሪያቸው “የውኃ አካል እና ኢትዮጵያ “ለዘላለሙ ተነጣጥለው መኖር አይችሉም”፣ ነገር ግን ድርድር አሁንም መንግሥታቸው የሚያስቀድመው አማራጭ እንደሆነ፤ ሌላኛው ያሉት አካል ይህንን መቀበሉ “የግድ ነው”፣ ካልሆነ ግን “በባሌም ሆነ በቦሌ አይቀርም” ማለታቸው፣ ሆኖም ከዚያ በመለስ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ወይን ከሕዳሴ ግድብ ድርሻ በመውሰድ፣ በቦታ ልውውጥ ወይም ሊዝን በመሳሰሉ የንግድ ሕጎች ኢትዮጵያ የባሕር በር ተጠቃሚ እንድትሆን በተናገሩ ማግስት ነው።
የሰላምና ደኅንነት ባለሙያው የደብዳቤው ይዘት “ሊመጣ የሚችል” ያሉትን ችግር በሆነ መንገድ “የሚጠቁም” ጭምር ነው።
የቆየው የሁለቱ ሀገራት የቃላት ምልልስ እና የግንኙነት መሻከር
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጥር 6 ቀን 2018 ዓ.ም ባጋራው አንድ መረጃ የኤርትራ መንግሥት “የሀገራችንን ሰላም ለማደፍረስ” ፅንፈኛ ያለውን “የፋኖ ቡድንን ለማስታጠቅ በስውር የላከውን ከ56 ሺህ በላይ የተለያዩ የጦር መሣሪያ ጥይቶችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን” ገልፆ ነበር። በወቅቱ የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር ይህ መረጃ “ውሸት ነው” ሲሉ ያስተባበሉ ሲሆን በኤርትራ ላይ ለመክፈት ለታቀደ ላሉት ጦርነት ቅድመ ሁኔታ አድርገው እንደሚመለከቱት ጠቅሰው ነበር።
የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት በዚያው ሰሞን ለኤርትራ ቴሌቪዥን በሰጡት ቃለ ምልልስ ደግሞ ኤርትራ ጦርነት እንደማትፈልግ ነገር ግን “ሀገራቸንን እንዴት መጠበቅ እንዳለብን እናውቃለን” ማለታቸው አይዘነጋም።

ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድም ኢትዮጵያ የቀይ ባሕር በር ያጣችበት “ስህተት” መስተካከል አለበት የሚል አቋም አራምደዋል። ይህም የሀገራቱን የቃላት ምልልስ ከፍ አድርጎት ቆይቷል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደብዳቤ “የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት እንዲከበር” የቀረበው ጥያቄ ተገቢ መሆኑ በዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች የሚደገፍ መሆኑን የሰላምና ደኅንነት ባለሙያው ያምናሉ።
እኒሁ ባለሙያ የደብዳቤው ዓላማ ከሌላ ዕይታም ሊተነተን እንደሚችል ጠቅሰዋል። “የደብዳቤው አላማ ይህ ነው ወይ?” ሲሉ ይጠይቃሉ።
የግንኙነት መሻከሩ የሚኖረው ቀጣናዊ ተጽዕኖ ምን ይሆን?
በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ግንኙነት መሻከር ዙሪያ ከዚህ በፊት ከዓለም አቀፍ ሕግ እና ከዲፕሎማሲ አንጻር ምልከታቸውን ያጋሩን ሌላ ተንታኝ “ሁለቱ ሀገራት በቀጥታ ወደ ግጭት ባይገቡም አንድም የሁለቱ ሀገራት መንግሥታት የየሃገራቱን ታጣቂዎችን በትጥቅም፣ በሰው ኃይልም የመደገፍ ሁኔታ ውስጥ ሊገቡ እንደሚችሉ፣ በሌላ በኩል ሳውዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች በቀጣናው የበላይ ሆኖ ለመውጣት ይህንን የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ “የጦርነት ሜዳቸው እንዳያደርጉት ሥጋት አለኝ” ብለዋል። የሰላምና ደኅንነት ባለሙያውም በዚህ ይስማማሉ።
“እንደ ቀጣናውም ስታይ ሌላ ጦርነት የሚያስተናግድበዛአቅም፣ ትከሻ ስለሌለው ይህን እንደተጨማሪ ሊከሰት የሚችል ዉጊያ፣ ጦርነት ለማስቀረት የሚችሉ አማራጮች በሙሉ መፈለግ አለባቸው።”
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደብዳቤ ምናልባትም የፊታችን ቅዳሜ እና እሑድ የካቲት 7 እና 8 በሚደረገዉ 39ኛ የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ጉዳዩን “አጀንዳ እንዲያደርገው” ቀድሞ ነጥብ የማስያዝ አካሄድ ይሆን እንደሆን ምልከታቸውን የጠየቅናቸው የሰላምና ደኅንነት ባለሙያው እንደዚያ ከታሰበም “ጥሩ ነው” ብለዋል።
የኤርትራ መንግሥት የሰጠው ምላሽ
የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ዛሬ ባወጣው መግለጫ “የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትናንት በኤርትራ ላይ የሰነዘረው “የውሸት እና የፈጠራ ውንጀላ” ነው ብሏል።
ደብዳቤውንም “በድምፅ እና በይዘቱ ፣ በተነሳሽነቱ እና በአጠቃላይ ዓላማው አስደናቂ ነው” ሲል ውድቅ አድርጎታል።
መግለጫው አክሎም የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይን ደብዳቤ በኤርትራ ላይ ከሁለት ዓመታት በላይ በቆየው ባለው “የጥላቻ ዘመቻ ዘዴ እና አዙሪት ውስጥ ሌላ አሳዛኝ ተግባር ነው።” ይላል።
ቀደም ተብሎ እንደተገለፀው “የኤርትራ መንግሥት ነዳጅ ለመጨመር [በጉዳዩ ላይ] እና ኹኔታውን ለማባባስ ትርጉም የለሽ ያለው ውዝግብ ውስጥ ለመሳተፍ ምንም ተነሳሽነት ወይም ፍላጎት የለውም።” ብሏል። https://www.dw.com/am/