የተመድ የሕጻናት መብት ተከታታይ ኮሚቴ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ግድያዎችን፣ የጾታ ጥቃቶችን፣ እገታዎችንና የሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽነት አለመኖርን ጨምሮ በሕጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጥሠቶች በከፍተኛ ደረጃ መጨመራቸው “አስደንጋጭ” እንደኾነበት ገለጠ። ኮሚቴው፣ ኢትዮጵያ በሕጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጥሠቶችን እንድታስቆም፣ እንድትከላከልና ለሕጻናት ሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ እንድታደርግ የኢትዮጵያን የሕጻናት መብት ይዞታ ከገመገመ በኋላ ሰሞኑን ባወጣው ሪፖርት ጠይቋል። በካምፖች ውስጥ የተያዙ ሕጻናትን ለመለየት መንግሥት ባስቸኳይ እንዲፈቅድ የጠየቀው ኮሚቴው፣ በዚህ ድርጊት እጃቸውን ያስገቡ አካላት ተጠያቂ እንዲሆኑም አሳስቧል። መንግሥት ብሄራዊ የሕጻናት ጥበቃ ሕግ እንዲያወጣ፣ በሕጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን አጠናቅሮ የሚይዝ ብሄራዊ የመረጃ ቋት እንዲፈጥር፣ በሕጻናት ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶች በገለልተኛ አካል እንዲጣሩ እንዲያደርግና አጥፊ አካላትን በሕግ እንዲጠይቅ ጭምር ኮሚቴው ጠይቋል።