አገዛዙ የግንኙነት መስመሮችን ዘግቶ ሲቪሊያንን በመጨፍጨፍ ላይ ይገኛል
የካቲት 01 ቀን 2018 ዓ.ም
ከአፋብን የተሰጠ መግለጫ
ትላልቅ ከተሞችን የሚያገናኙ አውራ መንገዶችን በመዝጋት በህዝቡ ላይ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ምስቅልቅል ሲያደርስ የቆየው የብልፅግና አገዛዝ በከባድ መሳሪያወች ሲቪሊያንን በመጨፍጨፍ ላይ ይገኛል።
ከጥር 26 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት ቀናት በጀኔራል አድማሱ አለሙ እና በጀኔራል ዘውዱ ሰጥአርጌ የሚመራው 11ኛ ዕዝ እና ቀጠናው ላይ የተሰማራው ሪፐብሊካን ጋርድ ደቡብ ወሎ ዞን ወግዲ ወረዳ የተለያዩ ቀበሌወች ድሮን፣ ቢኤም እና መድፍን በመጠቀም ከ 100 (አንድ መቶ) በላይ ንፁሃንን በግፍ ጨፍጭፏል፤ ከአርባ በላይ መኖሪያ ቤቶችን ሙሉ በሙሉ አውድሟል፤ በርካታ ቁጥር ያላቸው የቤት እንስሳትን ገድሏል።በዚህ ጥቃት የአንድ ቤተሰብ ስድስት አባላትም በቤታቸው ባሉበት ተጨፍጭፈዋል።
በተመሳሳይ ግዜ ውስጥ በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳም የአገዛዙ ሰራዊት ከኦሮምያ ልዩ ዞን ታጣቂወች ጋር በመቀናጀት በፈፀመው ጭፍጨፋ በበርካታ ሲቪሊያን ላይ የከባድ መሳሪያ ድብደባ በማድረግ ከ20 በላይ ንፁሃንን ገድሏል፤ በርካታ ቤቶችን አውድሟል፤ እንዲሁም የቤት እንስሳትን ዘርፏል። በምስራቅ ጎጃም ሸበል በረንታ ወረዳም ምንም አይነት ውጊያ በሌለበት የአርሶ አደር መንደሮችን በመድፍ ደብድቧል።
በመሆኑም ይህ አረመኔ አገዛዝ እንደ ህዝብ ያወጀብንን የዘር ማጥፋት ጦርነት መመከት ብሎም መቀልበስ አማራጭ የሌለው የትውልዱ ግዴታ በመሆኑ ከመቼውም ጊዜ በላይ መላው ህዝባችን ለህልውናው በጋራ እንዲታገል ጥሪ እናቀርባለን።
በተጨማሪም የስልክ እና የኢንተርኔት ግንኙነቶችን በሰሜን ሸዋ፣ በምስራቅ ጎጃም እና በደቡብ ወሎ አዋሳኝ ቦታወች ሙሉ በሙሉ በመዝጋት አረመኔው አገዛዝ በንፁሃን ላይ ያነጣጠሩ ተመሳሳይ ወንጀሎችን በመፈፀም ላይ ስለሆነ መሠል ጥቃቶችን ለመከላከል ህዝቡ አስፈላጊዉን ጥንቃቄ እንዲያደርግ እናሳስባለን።
አገዛዙ የዓለም አቀፍ የጦርነት ህግ መሰረታዊያን የሆነውን ንፁሃንን ከጥቃት የመጠበቅ ግዴታን በመተላለፍ የዘር ማጥፋት ወንጀል እየፈፀመ በመሆኑ የአፍሪካ ህብረት፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋማት፣ የተባበሩት መንግስታት እንዲሁም በአማራ ህዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለው ዘር ማጥፋት የሚገዳችሁ እና ጉዳዩ የሚመለከታችሁ አካላት ሁሉ ይህንን የጦር ወንጀል በመቃወም የሰብአዊነት ግዴታችሁን እንድትወጡ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ