የፎቶው ባለመብት, Gamo Zone Communication
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ስር ሚገኘው ጋሞ ዞን “በትምህርት ሚኒስቴር የተዘጋጁ” የ9ኛ እና 11ኛ ክፍል የታሪክ መጽሐፍት “የጋሞ ብሔር አንድነት ላይ አደጋ የሚጥሉ የውሸት ታሪኮችን” ይዘዋል ሲል ከሰሰ።
የዞኑ ትምህርት ቢሮ “የግል የፖለቲካ ፍላጎታቸውን በመጽሐፍ መልክ ያሳተሙ” ሲል የገለጻቸው አዘጋጆች እና አርታኢዎች “በሕግ እንዲጠየቁ” አሳስቧል።
የጋሞ ዞን ትምህርት መመሪያ “የውሸት ታሪኮችን” ይዘዋል ያላቸው የ9ኛ እና የ11ኛ ክፍል የታሪክ መጽሐፍት አንዳንድ ክፍሎች ለተማሪዎች እንዳይሰጡ ትዕዛዝ ያስተላለፈው ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ጥር 21/2018 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ ነው።
የትምህርት መመሪያ ኃላፊው ዶ/ር አዲሱ አዳሙ ይህንን ትዕዛዝ የያዘው ደብዳቤ በዞኑ ስር ለሚገኙት 14 የወረዳ እና ሰባት የከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤቶች መጻፉን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
ይህን ቅሬታ ለክልሉ ትምህርት ቢሮ መቅረቡንም የተናገሩት ዶ/ር አዲሱ “ከክልል ጋር ግንኙነት እየፈጠርን ነው ያለነው፤ ክልሉ የማስተካከያ እርምጃ ይወስዳል ብለን እንጠብቃለን” ብለዋል።
ለደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ ግልባጭ የተደረገው የዶ/ር አዲሱ ደብዳቤ፤ እንደሚያመለክተው ቅሬታ የተነሳባቸው መጽሐፍት በአውሮፓውያኑ 2023 በትምህርት ሚኒስቴር የታተሙ ናቸው።
የዞን ትምህርት መመሪያ ኃላፊው፤ በእነዚህ “መጽሐፍት ውስጥ የጋሞ ብሔር አንድነት ላይ አደጋ የሚጥሉ የሚከተሉት የውሸት ታሪኮች ታሪኮች ተቀነባብረዋል” ሲሉ በደብዳቤያቸው ጽፈዋል።
ደብዳቤው በቀዳሚነት ያስቀመጠው በ9ኛ እና በ11ኛ ክፍል የታሪክ መጽሐፍት “የኦሞቲክ ቋንቋ ተናጋሪ ሕዝቦች” በሚል ምሳሌ ሲጠቅስ “ጋሞ እና ዶርዜ” ማለቱ ነው። “ዶርዜ የጋሞ አንዱ ደሬ (ማኅበረሰብ/community) ሲሆን ቋንቋውም የጋሞኛ አንዱ ዘዬ (dialect)” እንደሆነ ደብዳቤው ያስረዳል።
የዞኑ ትምህርት መምሪያ “ከይዘቱ ውስጥ ዶርዜ የሚለውን በማውጣት ትምህርት እንዲሰጥ” በስሩ ላሉት መዋቅሮች ትዕዛዝ አስተላልፏል። ተመሳሳይ ማስተካከያ እንዲደረግ የታዘዘበት ሌላኛው ጉዳይም በ11ኛ ክፍል የታሪክ መጽሐፍ ላይ ተካትቷል የተባለ ነው።
የጋሞ ዞን ትምህርት መመሪያ ቅሬታ ያነሳበትን አንድ የመጽሐፉን አንቀጽ በደብዳቤው ላይ አስፍሯል። በእንግሊዘኛ የተጻፈው ይህ ክፍል “የኦሞቲክ ሕዝብን” የሚዘረዘዝር ነው። “ዶርዜ፣ ወላይታ፣ የም፣ ከፋ፣ ዲዚ፣ ቤንች” እና ሌሎች በዚህ ክፍል ላይ ተዘርዝረዋል።
በዚህ ዝርዝር ውስጥ ‘ዶርዜ’ ተብሎ መጠቀሱን የትምህርት መመሪያው ተቃውሟል። “የተከበረውን የጋሞን ብሔር ሆን ብሎ በመተው ዶርዜ በማለት ከፋፋይ እና የውሸት ታሪክ ለመትከል የተጣለ እንጂ የትምህርት ይዘት [አይደለም]” ሲል በጠንካራ ቃላት ትችቱን ሰንዝሯል።
“ዶርዜ የጋሞ አንዱ ደሬ (community)” መሆኑን በድጋሚ አጽንኦት የሰጠበት የትምህርት መመሪያው፤ ትምህርት ቤቶች “ዶርዜ የሚለውን በማውጣት በምትኩ ጋሞ የሚለውን በማስገባት” እንዲያስተምሩ አዝዟል።
በተጨማሪም የ11ኛ ክፍል መጽሐፍ ላይ “የወላይታ ማላ ስርዎ መንግሥት እንደ ጋሞ፣ ቁጫ፣ ቦሬዳ እና ደውሮ ባሉ አጎራባች ሕዝቦች ላይ ተጽኖውን አስፋፍቷል” በሚል የተጻፈው ክፍል ላይ ተመሳሳይ ትችት አንስቷል። “ወላይታ የጋሞ ሕዝብ ጎረቤት እንጂ በጋሞ ሕዝብ ላይ ያሳደረው ታሪካዊ ተጽእኖ [አልነበረም]” ሲል ቀዳሚ ያለውን “የውሸት ታሪክ” ጠቅሷል።
“በሁለተኛ ደግሞ የጋሞ ብሔር አካል የሆኑትን ቦረዳ እና ቁጫን በተለየ ዝርዝር በምሳሌነት አስቀምጧል” ሲል የወቀሰው የዞኑ ትምህርት መመሪያ፤ ይህ አረፍተ ነገር “ሙሉ በሙሉ ከይዘቱ ተወግዶ” ትምህርት እንዲሰጥ አሳስቧል።
መጽሐፍቱ “ለትውልድ የውሸት ታሪክ በማስተማር የጋሞ ብሔር አንድነት ላይ ጥቃት” ሰንዝረዋል ሲል ከስሷል። የመጽሐፍቱ “አዘጋጆች እና አርታኢዎች የግል ፖለቲካ ፍላጎታቸውን በመጽሐፍ መልክ ያሳተሙ መሆናቸውን ተረድተናል” ሲልም ወንጅሏል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ እና የሚመለከታቸው አካላት “በአስቸኳይ ማስተካከያ” እንዲያደርጉ ጠይቋል። “በመጽሐፍ ዝግጅት እና አርትኦት ሥራ ላይ የተሳተፉ ግለሰቦችም ቢሆኑ በሕግ እንዲጠየቁ” አሳስቧል።
የጋሞ ዞን የትምህርት መመሪያ ኃላፊው ዶ/ር አዲሱ ከክልሉ መንግሥት “ምላሽ እየጠበቁ” መሆናቸውን በመጥቀስ ተጨማሪ ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ቢቢሲ ከትምህርት ሚኒስቴር እና ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ በጉዳዩ ላይ አስተያየት ለማግኘት ቢሞክርም ወዲያው ምላሽ ማግኘት አልቻለም።