ኤርትራ፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ንግግር “የጦርነት አጀንዳን ምክንያታዊ ለማድረግ” የቀረበ ነው አለች

የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስለ ኤርትራ መንግሥት ያደረጉት ንግግር፤ የኢትዮጵያ መንግሥት “በኤርትራ ላይ ሊከፍት ያቀደውን የጦርነት አጀንዳ ምክንያታዊ ለማድረግ” የቀረበ ነው ሲሉ ተቹ።

የኤርትራ መንግሥት ቃል አቀባዩ ማክሰኞ ጥር 26/2018 ዓ.ም. ምሽት በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ጦርነት “ወቅት እና ከጦርነቱ ረጅም ጊዜ በኋላ ለኤርትራ ሠራዊት የክብር ሜዳይ” ሲሰጥ ነበር ብለዋል።

የማነ ይህንን ያሉት፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ በትግራይ ጦርነት ወቅት የኤርትራ ወታደሮች የጅምላ ግድያን ጨምሮ የተለያዩ ግፎችን ፈጽመዋል በሚል ከወነጀሉ በኋላ ነው።

የኤርትራ እና የኢትዮጵያ ግንኙነት መሻከርን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ በሁለቱ አገራት መካከል ግንኙነት ውስጥ ችግር የተፈጠረው መንግሥታቸው በቀይ ባሕር ላይ የባሕር በር የማግኘት ጥያቄን በማንሳቱ “እንዳልሆነ” ተናግረዋል።

“በትግራይ ውጊያ ሲጀመር በመጀመሪያው ዙር ወጊያ ሽሬን ካስለቀቅን በኋላ የኤርትራ ጦር ከኋላ ኋላ ተከትሎ ሽሬ ገብቶ የአንዳንድ ግለሰቦችን ቤት ማፍረስ፣ ፎቅ ማፍረስ ሲጀምር ፀብ ተጀምሯል፤ አልተናገርንም እንጂ” ሲሉ በሁለቱ መንግሥታት መካከል “ጸብ የጀመረው” ከትግራይ ጦርነት ጋር በተያያዘ መሆኑ ገልጸዋል።

በተጨማሪም የኤርትራ ወታደሮች አክሱም ውስጥ “ወጣቶችን በጅምላ መረሸናቸውን” እንዲሁም አድዋ እና አዲግራት ከተሞች ውስጥ ፋብሪካዎችን እንዳወደሙ እና እንደዘረፉ ለምክር ቤቱ አባላት ተናግረዋል። እነዚህን ድርጊቶች ለማስቆም ወደ ኤርትራ “በርካታ መልዕክተኞችን መላካቸውን” አክለዋል።

“ይሄ ጸብ ተፋፍሞ ሄዶ የፕሪቶሪያ ስምምነት ሲፈረም ‘እንዴት ህወሓት ሳይጠፋ፣ እንዴት ትግራይ ሳይወድም ፊርማ ይደረጋል?’ በሚል ነው ጸቡ የመጨረሻ ጫፍ የደረሰው” ብለዋል። “ከዚህ ኃይል ጋር ሆነው ነው እንግዲህ አንዳንድ የህወሓት ሰዎች ኢትዮጵያን ለማፍረስ እንሥራ ያሉት” ሲሉም ከስሰዋል።

ለዚህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር በኋላ በኤክስ ገጻቸው ምላሽ የሰጡት የኤርትራ መንግሥት ቃል አቀባይ አቶ የማነ፤ የብልጽግና ፓርቲ “አስቀያሚ መለያ የሆነው ማጭበርበር እና አታላይነት ዛሬ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ታይቷል” ብለዋል።

“የብልጽግና ፓርቲ መሪ እና ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዦቹ” በትግራይ ጦርነት እየተካሄደ በነበረበት ወቅት እና ጦርነቱን ከቆመ በኋላ “ለረጅም ጊዜ ለኤርትራ ሠራዊት ከፍተኛ ውዳሴ” ሲያቀርቡ ነበር ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት አመራር እና ወታደራዊ አዛዦች “ጥልቅ ምሥጋናቸውን ለመግለጽ በአገር ደረጃ ሜዳሊያዎችን ሲያበረክቱ እንደነበር በሕዝብ የሚታወቅ መሆኑ ይታወሳል” ሲሉም በኤክስ ገጻቸው ጽፈዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ ባደረጉት ንግግር የዘረዘሯቸውን ጉዳዮች “ርካሽ እና ወራዳ ውሸት” ሲሉም አጣጥለዋል።

በኤርትራ ላይ የቀረበው ክስ የኢትዮጵያ መንግሥት “ሉዓላዊ የባሕር በር ማግኘት በሚል ሽፋን በኤርትራ ላይ ሊከፍት ያቀደውን የጦርነት አጀንዳ ለመሸፈን እና ምክንያታዊ ለማስመስል በድፍረት የተቀረጸ” ነው ሲሉም ወቅሰዋል።

የማነ አስከትለው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በፓርላማ ንግግራቸው ያነሱትን እስራኤል ከሶሪያ በወረራ የያዘቻቸውን የጎላን ከፍታዎች ጉዳይ ጠቅሰዋል።

ዐቢይ በማብራሪያቸው ስለ መንግሥታቸው የቀይ ባሕር ጥያቄን እንደ የብሔራዊ አጀንዳ እንደሚገነዘበው ተናግዋል።

የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል

“እስራኤል የጎላን ተራራን የያዘችው ለብሔራዊ ደኅንነቴ፣ ለህልውናዬ ችግር ያጋጥመኛል ብላ ስላመነች ነው” ያሉት ዐቢይ፤ አክለውም “ቀይ ባሕር እና ኢትዮጵያ ለዘላለሙ ተነጣጥለው መኖር አይችሉም” ሲሉ ተደምጠዋል።

ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ የባሕር በር ለማግኘት የምትፈልገው “በቢዝነስ ሕግ” እንደሆነ ተናግረዋል። በባሕር በር ምትክ የታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ወይም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ድርሻ ሊቀርብ እንደሚችል ጠቁመዋል። ይህ ካልሆነም “በሊዝ” ወይም “በመሬት ልውውጥ” ሊከናወን እንደሚችልም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ እያለ ያለው “በስምምነት በገበያ ሕግ፣ ሳንጠፋፋ አብረን ለማደግ በድርድር እንፍታው እያለ ነው” ሲሉም የመንግሥታቸውን አቋም ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ኢትዮጵያ አሰብ ላይ “ወደብ፣ አየር ማረፊያ፣ መንገድ፣ ነዳጅ ማጣሪያ” መገንባቷን አስታውሰዋል።

“ለእኛ የሚገባንን በሆነ በሆነ ምክንያት ዛሬ መከልከል ቢታሰብ በቀጣይነት ማስቀረት ስለማይቻል ወደ ማይፈለግ ነገር ሳይገባ በሰላም በድርድር መጨረስ ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ” ብለዋል።

ዐቢይ የጠቀሱትን የጎላን ከፍታዎች ምሳሌ ያነሱት የኤርትራው የማስታወቂያ ሚኒስትር፤ ይህ ጉዳይ መነሳቱ የኢትዮጵያ መንግሥት አሥመራ ላይ ሊከፍት ያቀደውን “ግድየለሽ እና ሕገ ወጥ የጦርነት አጀንዳ ምክንያታዊ ለማድረግ” የቀረበ እንደሆነ ጽፈዋል።

“እንዲያውም [የብልጽግና ፓርቲ] መሪ በኤርትራ ላይ የያዘውን ግድ የለሽና ሕገ-ወጥ የጦርነት አጀንዳ ምክንያታዊ ለማድረግ [በሚል] በዚሁ ንግግሩ ላይ ‘የጎላን ከፍታዎች ምሳሌን’ ሲያነሳ ጨዋታውን ራሱ አጋልጦታል” ብለዋል።

ከፕሪቶሪያ ስምምነት መፈረም ወዲህ ግንኙነታቸው እየሻከረ የመጣው ኢትዮጵያ እና ኤርትራ፤ አንዳቸው ሌላኛቸውን ሲወነጅሉ ቆይተዋል።

ከሳምንት በፊት የፌደራል ፖሊስ የኤርትራ መንግሥት በአማራ ክልል ለሚንቀሳቀሱት ፋኖ ኃይሎች “ልኳቸዋልል” ያላቸውን የጦር መሳሪያዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል። ኤርትራ ግን ይህንን ውንጀላ ውድቅ አድርጋለች።