በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች ከትላንት በስቲያ ሰኞ ጥር 25 አመሻሽ ጀምሮ በዞኑ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ቡድኖችን ላይ የጸጥታ ዘመቻ ለማካሄድ በሚል ኔትዎርክ መቋረጡ ተሰምቷል።
በዞኑ ኔትዎርክ ከተቋረጠባቸው ወረዳዎች መካከል ወረ ጃርሶ፣ ኩዩ፣ ደገም እና ሂደቡ አቦቴ እንደሚገኙበት ምንጮች ተናግረዋል።
ከሰሞኑ በርካታ ቁጥር ያላቸው የመከላከያ ሠራዊት አባላት እና የክልሉ ፖሊስ ወደ ዞኑ የገቡ ሲሆን፣ ይህንኑ ተከትሎ ለጸጥታ ዘመቻው ይረዳ ዘንድ የበይነ መረብ፣ የሞባይል ድምጽ እንዲሁም የመልእክት አገልግሎቶች በተጠቀሱት ወረዳዎች ሙሉ ለሙሉ እንዲቋረጥ መደረጉን ታውቋል።
ከዚህ ቀደምም፣ በዞኑ በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች ለተመሳሳይ የጸጥታ ዘመቻ ሲባል ለወራት ኔትዎርክ ሙሉ ለሙሉ ተቋርጦ እንደነበር ይታወሳል።