ምርጫ ቦርድ ሕወሓትን ከፖለቲካዊ እንቅስቃሴ አገደ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕ.ወ.ሓ.ት) በሚቀጥሉት ሦስት ወራት ምንም አይት የፖለቲካ እንቅስቃሴ እንዳያደርግ እግድ ጣለ፡፡ በነዚህ የዕግድ ጊዜ የዕርምት ዕርምጃ ሳይወስድ ቢቀር የፖርቲው ምዝገባ እንደሚሰረዝም አስታውቋል።

ሕ.ወ.ሓ.ት በሽብር እንቅስቃሴ ተሳትፏል በሚል በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአሸባሪነት ዝርዝርዝር ውስጥ ከተመዘገበ እና ህጋዊ ህልውናውን ካጣ በኋላ በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሠረት በልዩ ሁኔታ ነሃሴ 3 2016 ዓ.ም የተመዘገበ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ህጋዊ ሆኖ ከተመዘገበ ጊዜ አንሥቶ ባሉት ሥድስት ወራት ውስጥ የቦርዱ ታዛቢዎች በተገኙበት ጠቅላላ ጉባዔ ማድረግ ይጠበቅበት የነበረ ቢሆንም፣ ቦርዱ እውቅና የሰጠው እና በታዛቢነት የተሳተፈበት ጉባዔ ሳያደርግ ቀርቷል።

በመሆኑም ቦርዱ፥ ታኅሣሥ 17 ቀን 2017 ዓ.ም በፃፈው ደብዳቤ ፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔ የማድረጊያ ጊዜ ገደቡ ሊጠናቀቅ ከሁለት ወር ያነሰ ጊዜ አንደቀረው በመግለጽ በሕግ የተጣለበትን ግዴታ አንዲፈጽም ማሳሰቡን አስታውሷል።

ይህንን የሕግ ግዴታ በወቅቱ ሳይፈጽም ቢቀር ቦርዱ ሕጉን መሠረት በማድረግ ተገቢ ነው የሚለውን ውሣኔ የሚሰጥ መሆኑን መግለጹንም አክሏል።

ይሁንና ፓርቲው የፓርቲው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ-ምግባር ዐዋጅ ቁጥር 1162/2011 እና ዐዋጁን ተከትሎ የወጣውን መመሪያ እና ደንጋጌዎች፣ እንደዚሁም የቦርዱን ውሣኔዎች በማክበር የጠቅላላ ጉባዔ ሳያካሄድ፣ መተዳደሪያ ደንቡን ሳያፀድቅ እና አመራሮቹን ሳይመርጥ በሕግ የተሰጠው የሥድስት ወር ጊዜ ተጠናቅቋል።

በዚህ መሠረት ቦርዱ የካቲት 4 ቀን 2017 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ የሕ.ወ.ሓ.ትን ጉዳይ መርምሮ የሚከተሉትን ውሳኔዎች አሳልፏል፦
1ኛ. ፓርቲው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ-ምግባር ዐዋጅ እና ዐዋጁን ተከትሎ የወጣውን መመሪያ ላይ የተመለከቱ ድንጋጌዎችን ባለማክበር ጉልህ ጥሠት በመፈጸሙ ይህ ውሣኔ ከደረሰው ቀን ጀምሮ ለሦስት ወራት በምንም ዓይነት የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ አንዳይሣተፍ እንዲታገድ ወሥኗል።

2ኛ. ፓርቲው ለእግዱ ምክንያት የሆነውን ጥሠት በማረም፤ ዐዋጁን፣ ዐዋጁን ተከትሎ የወጣውን መመሪያ፣ የቦርዱን ውሣኔዎችና ትዕዛዞች በማክበር ፖርቲው ሊያደርግ የሚገባውን ጠቅላለ ጉባዔ ለማድረግ የሚያስችለውን የጉባዔ ቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ለመሥራት ለቦርዱ በጽሑፍ ሲያሳውቅና ቦርዱ ይህንኑ ሲያረጋግጥ በመመሪያው መሠረት ቦርዱ ዕግዱን የሚያነሣ መሆኑን ወሥኗል።

3ኛ. ፖርቲው በተሰጠው የሦስት ወራት የዕግድ ጊዜ የዕርምት ዕርምጃ ሳይወስድ ቢቀር የተለየ አካሄድ ሳይከተል የፖርቲው ምዝገባ እንዲሠረዝ ወሥኗል።

ሃምሳኛ ዓመቱን የምሥረታ በዓል ለማክበር በተዘጋጀበት ዋዜማ ላይ የሚገኘው እና እንዲህ አይነት ውሳኔ የተላለፈበት ሕ.ወ.ሓ.ት ኢትዮጵያን ለ27 አመታት ያስተዳደረ እና በድርጅታዊ ጥንካሬው እንደዚሁም ጥብቅ የአባላት ሥነምግባር የሚታወቅ ሲሆን፣ የረጅም ጊዜ ሊቀመንበር ከሆኑት መለስ ዜናዊ ህልፈት በኋላ የሚታወቅበትን ድርጅታዊ ማንነት እና ቁመና አጥቶ አንደሚገኝ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፓርቲው የገባበት ክፍፍል ዐቢይ ማሳያ ነው፡፡

ደም አፋሳሽ የነበረው የተግራይ ጦርነት አልፎ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር በፕሪቶሪያ የሠላም ሥምምነት ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ህይወት የቀጠፈው ጦርነት የተቋጨ ቢሆንም፣ በፓርቲው ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረፂዮን ገ/ሚካኤል እና በጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ መካከል የተፈጠረው ፍጥጫ ፓርቲውን በታሪኩ አይቶ ወደማያውቀው ቀውስ እየወሰደው እንደሆነ ይታወቃል፡፡