ምሥራቅ አርሲ ውስጥ አኹንም በዝምታ ንጹሓን በማለቅ ላይ ናቸው!

ምሥራቅ አርሲ ውስጥ አኹንም በዝምታ ንጹሓን በማለቅ ላይ ናቸው!
ቅዳሜ ጥር 24 ቀን 2018 ዓ.ም በምሥራቅ አርሲ ዞን ሆንቆሎ ወረዳ ሌሙ ለማን ቀበሌ፣ 13(አሥራ ሦስት) የጉራዮ እግዚአብሔር አብ ቤተክርስቲያን አጥቢያ ምዕመናን ታግተው ተወስደዋል። እስከአኹን አንድ ሰው የተለቀቀ ሲኾን አንዱ ታጋች ሕጻን ልጅ ነው፤ አባቱን ፈልገው ሲያጡ ነው ሕጻኑን የወሰዱት ብለውናል አንድ የአካባቢው ነዋሪ።
እዚያው ም/አርሲ ጉና ወረዳ፣ አሰኮ ላይ ጥር 25 ቀን 2018 ዓ.ም የተገደሉ ሰዎች አሉ፡፡ ቀርበን ማጣርት አስቸጋሪ በመኾኑ ቊጥራቸውንና ማንነታቸውን መለየት አልቻልንም ብለውናል፡፡
በዚያው ምሥራቅ አርሲ፣ መርቲ ወረዳ፣ ፈረቀሳ ጃዊ ቀበሌ ኅዳር 23 ቀን 2018 ዓ.ም ምሽት 2:00 ገደማ አቶ ጌታሁን ገ/መድኅን የተባሉ የአካባቢው ነዋሪ ደጃቸው ድረስ በመምጣት ለማየትም ለመስማትም በሚዘገንን ኹኔታ ገድለዋቸው፣ ንብረታቸውን ዘርፈው፣ ከብቶቻቸውን ነድተው ወሰደዋል። ሕጻናትን ጨምሮ ያስተዳድሯቸው የነበሩ ከአሥር በላይ ቤተሰብም ተበትኗል። ፍትሕ ቢቀር ለሕጻናቱ ማሳደጊያ ንብረቱ እንዲመለስ ጥረት እንዲደረግ ለአካባቢው ፀጥታ አካላት ውትወታ ቢደረግም እንዳልሰሙ አልፈውታል፣ ቤተሰቡም ከፍተኛ ችግር ላይ መኾኑን ተረድተናል።
ፓርቲያችን ለክልሉ ባለስልጣናትም ለፌዴራል መንግሥትም በተደጋጋሚ ያሳሰበ ቢኾንም በተቀናጀና በተጠና መልኩ በአካባቢው የንጹሓን እልቂትና እገታ እንደቀጠለ ነው። ለዚያም ነው የብልጽግና መንግሥት በመሠረታዊ የመንግሥትነት መስፈርቶች ተፈትኖ የወደቀና ዝቅተኛውን/minimal/ መሥፈርት እንኳን የማያሟላ ሥርዓት ነው የምንለው።
ፓርቲያችን ለሞቱት ሐዘኑን እየገለጸ የታገቱት ያለምንም ቅድመ ኹኔታ እንዲለቀቁ አበክሮ ይጠይቃል። ዛሬ ፍትሕ እንደ ሰማይ ብትርቅ እጃቸው ያለበት የመንግሥት ባለስልጣናትና የጫካ ጌቶች በቅርብ ቀን በፍትሕ አደባባይ መቅረባቸው ግን አይቀሬ ነው።
ፈጣሪ አገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ!
እናት ፓርቲ
ጥር ፳፯ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ