ከተቃጣብኝ የግድያ ሙከራ ለጊዜው ብተርፍም ፣ መላው ቤተሰቤ ግን አሁንም አደጋ ላይ ነው

” እርምጃ ውሰዱበት ተብለናል” የአገዛዙ ፖሊሶች!

“ከተቃጣብኝ የግድያ ሙከራ ለጊዜው ብተርፍም ፣ መላው ቤተሰቤ ግን አሁንም አደጋ ላይ ነው” ዘሪሁን ገሠሠ!

የቀድሞው የአብን ፓርቲ መስራች አባልና አመራር የነበረው፡ በኋላም የሕዝቤን ጥያቄ በምስር ወጥ አለውጥም በሚል በአቋሙ በመፅናቱ ከእስራት ጀምሮ አያሌ ግፍና መከራ የተፈፀመበት ፖለቲከኛው ዘሪሁን ገሠሠ “ህዝብ_ይወቅልኝ” በሚል ትናንት ጥር 25/2018 ዓ/ም የተፈፀመበትን ግፍ በሚከተለው መልኩ ገልጿል።

ህዝብ_ይወቅልኝ!

በዛሬው እለት ማለዳ ለስራ ከወጣሁበት ስልክ ተደወለልኝ። ”አባቴ ቤታችንን ሊያፈርሱብን ነው!” የሚል የልጆቼ ድምፅ ነበር። የዛሬ ሁለት አመት በመከላከያ (ኮማንድ ፖስት) ተይዥ ወደአዋሽ አርባ ከመሄዴ በፊት ” አባቴ ኪራይ ቤቱን በ3 ቀን ለቃችሁ ውጡ ተባልን!” ብለው በገለፁልኝ የለቅሶ ድምፅ ነበር።

ከነበርኩበት በፍጥነት ደረስኩ። ስደርስ ግን ”ሀሰን” በሚባል አየር ማረፊያ አካባቢ በሚኖር የኮምቦልቻ ከተማ #ሚሊሻ የሚመራ የታጣቂ ቡድን ግሬደር አስገብቶ ማፍረስ ጀምሯል። ወጉ አይቀርምና ”በህግ  አምላክ!” ብዬ ለማስቆም ሞከርኩ።

” መላ ቤተሰቤን ገድላችሁ ካልሆነ ፣ በአመታት ጥረት በይዞታዬ ላይ የሰራሁትን ቤት ከህግ አግባብ ውጪና ተገቢውን ካሳ ሳትከፍሉ አታፈርሱም!” በማለትም ለማስረዳት ጣርኩ። ሀሰን የሚባለው የቡድኑ መሪ ግን ” እርምጃ ውሰዱበት ተብለናል። አይተኩሱም ብለህ እንዳታስብ!” በማለት አፈሙዝ ወደደረቴ አነጣጠረ። መላው የአካባቢው ማህበረሰብ ሁኔታውን በለቅሶ ታጅቦ ይከታተል ነበር።

”እሺ አፍርሱ” ብዬ ሂደቱን በካሜራዬ ለመቅረፅ ስጀምር ሁሉም የታጠቁ ሀይሎች በህብረት እላዬ ላይ ሰፈሩ። ባለቤቴን ጨምሮ የስድስት ወር ህፃን ልጄ ተፈነከተች። ግፍን ተሸክሜ ከምኖር መሞትንም በደስታ ስለምቀበለው ፣ በእኔ ላይ የደረሰውን ልተወውና መላው ቤተሰቤ ግን እጅጉን ተጎድቷል።

ግብግቡ ከቀጠለ በኃላ በበርካታ ታጣቂዎች ታግቼ ውያለሁ። ሂደቱ የቤቱን አጥር በማፍረስ ለጊዜው የቆመ ቢሆንም ፣ ”በቀጣይ ቀናት እናፈርሰዋለን!” የሚል ዛቻ ተነግሮኛል።

ለዚህ ሁሉ መነሻ የሆነው በአካባቢው የሚሰራው የአስፋልት መንገድ ሲሆን የመንግስት አመራሮች  ” ካሳ የምንከፍለው ገንዘብ የለንም። ገንዘብ ስናገኝ እንከፍላለን። መንገዱ ግን እስከምርጫው ማለቅ ስላለበት ፣ እናንተ  በ15 ቀን ውስጥ ቤታችሁን አፍርሳችሁ ጎዳና ውደቁ!” የሚል ውሳኔ ይዘው መምጣታቸውን ተከትሎ ሲሆን ፣ ሌሎች አርሶደሮችና ባለይዞታዎች በተባለው አግባብ ፈርተው ያለአንድ ብር ካሳ ሲያፈርሱ ፣ የኔ ልጆችና ቤተሰቦቼ ግን የምንወድቅበት ሌላ አማራጭ ስለሌለን ” በህግ አግባብ በተቀመጠው መልኩ ይፈፀም። አለበለዚያ እኛን ገድላችሁ ቤቱን በላያችን ላይ አፍርሱት” የሚል ውሳኔ በመወሰናችን ነው!

ምንም እንኳ መጠነኛ ጉዳት ባስተናግድም ከታጣቂዎቹ እገታ ለጊዜው ነፃ ወጥቻለሁ። መላው ቤተሰቤ ግን በዚህ ጨለማ ” ምን ቤት አለንና …”  ብለው ፤ በረንዳ ላይ እየተላቀሱ በስጋት ላይ መሆናቸውን ደውዬ አረጋግጫለሁ። ይህ ዛሬ የግድያ ሙከራ ያደረገ ቡድን ነገ ምን እንደሚያደርጋቸው አላውቅም!

ባለፉት ሁለት አመታት ውስጥ ብቻ – አግተው ከስራ አሰናበቱኝ ፣ ቤተሰቤን ከተከራየንበት ቤት እንዲወጡ በማድረግ ጎዳና በትነው የበቀል ጥማታቸውን ተወጡ ፣ ከአስር ወራት የአዋሽ አርባ ቆይታ በኃላ ከእስር ብወጣም ፣ ” የፌደራል ኮማንድ ፖስት ቢለቅህ እኛ እንፈልግሀለን” ተብዬ በጊዜው የተያዙብኝ ስልኮችና ሌሎች ንብረቶችን ጨምሮ እስካሁን አልተለቀቁልኝም። የባንክ አካውንቴ ከታገደ ሁለት አመት አለፈው። ”ልቀቁልኝ” ብዬ ስሄድ ” ስናፈላልግህ ነበር” ተብዬ ታሰርኩ ፣ መልሼ ተፈታሁ። በመጨረሻም አካባቢውን ለቅቄ መሄድን መረጥኩ።

አሁን ደግሞ ልጆቼን በገዛ ይዞታቸው ላይ ቤት ሰርቼ ”ከኪራይ ቤት ወጡ”  ስል  ሞልቶ አልፈስ ያላቸውን  የግፍ ቁና ሊሰፍሩ መጥተው ፣ ይህ ኢ-ሰብአዊና አረመኔያዊ ወንጀል ተፈፅሟል።

ይህን ከመቻል በላይ የሆነውንና አደባባይ ለማውጣት የተገደድኩበትን ግፍ ስለፍትህ የቆመ ሁሉ እንዲያውቅልኝ እፈልጋለሁ! ምናልባትም በእኔም ሆነ በቤተሰቤ ላይ ከዚህም የከፋ ነገር ቢከሰት ተጠያቂዎቹና ይህን የፈፀሙትን አካላትም ከወዲሁ ለማሳወቅ እወዳለሁ!