አብይ አህመድ IMF ስለ ኢትዮጵያ የ2026 የኢኮኖሚ እድገት ትንበያ አስቀምጧል ብለው ያቀረቡት አሀዝ የተሳሳተ ነው

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አይ ኤም ኤፍ (IMF) ስለ ኢትዮጵያ የ2026 የኢኮኖሚ እድገት ትንበያ አስቀምጧል ብለው ያቀረቡት አሀዝ የተሳሳተ ነው

/ኢትዮጵያ ቼክ/- ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ዛሬ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው የአለም አቀፍ ገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ኢትዮጵያ በያዝነው የአውሮፓውያኑ 2026 ዓ.ም ዘጠኝ ነጥብ ሶስት ፐርሰንት (9.3%) ታስመዘግባለች ብሎ ተንብዩዋል ብለው ለፓርላማ አባላት ገለፃ አድርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዘንድሮ የበጀት አመት የስድስት ወር አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ውሎ በያዝነው የፈረንጆች አመት ኢትዮጵያ 10 ፐርሰንት እድገት እንደሚኖራት መንግስታቸው እንደተነበየ አሳውቀዋል።

”አይ ኤም ኤፍ ምን አለ? የኛ ኦሪጅናል እቅድ 9.2 (ፐርሰንት) ነው፣ አይ ኤም ኤፍ የኢትዮጵያ 2026 እድገት 9.3 ፐርሰንት ይሆናል ብሎ ተንብይዋል፣ ኦሪጅናል ካቀድነው በ0.1 ፐርሰንት የተሻለ ማለት ነው። አሁን ካሰብነው 10.2 (ፐርሰንት) አንድ ፐርሰንት በታች በኛና በአይኤምኤፍ መካከል የትንበያ ልዩነት አለ” ብለው ጠ/ሚር አብይ ለፓርላማ አባሎች አስረድተዋል።

ይሁንና ኢትዮጵያ ቼክ በዚህ ዙሪያ ባደረገው ማጣራት መረጃው የተሳሳተ መሆኑን አረጋግጧል።

የአለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅቱ በኦፊሴላዊ የፌስቡክ ገፁ እንዲሁም በድረ-ገፁ ላይ ባለፈው ጥቅምት ያጋራው መረጃ እንደሚያሳየው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በተያዘው 2026 የፈረንጆቹ አቆጣጠር 7.1 ፐርሰንት እንደሚያስመዘግብ ይጠበቃል (ማስረጃ: https://www.facebook.com/share/p/1BnQq4J4m7/)

በተጨማሪም ተቋሙ ከዘጠኝ ቀን በፊት ባወጣው አዲስ ሪፖርት ላይ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት 7.1 ፐርሰንት እንደሚሆን እንደሚጠብቅ በድጋሜ አረጋግጧል (ማስረጃ: https://www.imf.org/en/countries/eth)

ተቋሙ ባወጣው አዲስ ሪፖርት መሰረት ከሰሀራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራት የአማካኝ እድገት 4.6 ፐርሰንት እንደሚሆን በፌስቡክ ገፁ ላይ ባጋራው መረጃ ላይ አስቀምጧል (ሊንክ: https://www.facebook.com/share/p/1Ap8J5xwPn/)

የመንግስት መረጃዎች ለህዝብ ሲቀርቡ ትክክለኛ ካልሆኑ በህብረተሰቡ ዘንድ ግርታን ሊፈጥር ስለሚችል ጥንቃቄ ይሻሉ።

የአይ ኤም ኤፍ ኦፊሴላዊ ትንበያ ምስል ተያይዞ ቀርቧል።

ኢትዮጵያ ቼክ