የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ በኒዠር ዋና ከተማ ኒያሚ አቅራቢያ በሚገኝ አንድ ዓለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ በተፈጸመ ጥቃት ሁለት ቦይንግ 737 አውሮፕላኖቹ “መጠነኛ” ጉዳት እንደደረሠባቸው ገለጠ።
በጥቃቱ ጉዳት የደረሠባቸው አውሮፕላኖች፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አጋር የሆነውና መቀመጫውን ቶጎ ያደረገው ‘ስካይ ኤርዌይስ’ በአየር መንገዱ አማካኝነት የተከራያቸውና በኢትዮጵያ ሲቪል አቬሽን የተመዘገቡ አውሮፕላኖች እንደኾኑ አየር መንገዱ ትናንት ምሽት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
አየር መንገዱ፣ ወደ ኒጀር የላከው የቴክኒክ ቡድን ጉዳት የደረሠባቸው አውሮፕላኖች በቅርቡ ጥገና ተደርጎላቸው ወደ በረራ መመለስ እንደሚችሉ ማረጋገጡንም ጠቅሷል።
በሳህል አገራት በስፋት የሚንቀሳቀሠው ኢስላሚክ ስቴት የተባለው የሽብር ቡድን፣ በአውሮፕላን ማረፊያው ላይ ጥቃቱን መፈጸሙን ገልጧል።