” አክሱምን ይዘን ስናልፍ አክሱም ገብቶ ወጣቶች በጅምላ ሲረሽን ጸብ ተፋፍሟል። ዓድዋን ይዘን ስናልፍ ዓድዋ ሄዶ ፋብሪካዎች ሲፈታ፣ ሲሰርቅ ጸብ ተጋግሏል ” – ጠ/ሚ ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) ስለኤርትራ
🔴 ” ጸቡ የተጀመረው ብዙዎች እንደሚያስቡት የቀይ ባህር ጉዳይ ሲመጣ አይደለም! ”
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) በዛሬው የፓርላማ ማብራሪያቸው፣ በሰሜኑ ጦርነት ወቅት ስለነበረው የኤርትራ ተሳትፎና የሕወሓት ጉዳይ እስከዛሬ በይፋ ያልተናነሩትን ተናግረዋል።
በዚህም ከኤርትራ ጋር ” ጸቡ የተጀመረው ” በቀይ ባህር ጉዳይ እንዳልሆነ ገልጸዋል።
ጠ/ሚ ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) ስለኤርትራ እና ሕወሓት ምን አሉ ?
” ኤርትራ ከተፈጠረች ጊዜ ጀምሮ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል Issue ነበር፤ ታውቃላችሁ። እኛ ከመጣን በኋላ አያስፈልግም፣ ይቅርብን ብለን መክረናል። አምስት አመት ለመምነናል።
ጸቡ የተጀመረው ብዙዎች እንደሚያስቡት የቀይ ባህር ጉዳይ ሲመጣ አይደለም።
በትግራይ ውጊያ ሲጀመር በመጀመሪያው ዙር ውጊያ ሽሬን ካስለቀቅን በኋላ የኤርትራ ጦር ከኋላ ኋላ ተከትሎ ሽሬ ገብቶ የአንዳንድ ግለሰቦች ቤት ማፍረስ፣ ፎቅ ማፍረስ ሲጀምር ጸብ ተጀምሯል፤ አልተናገርንም እንጂ።
አክሱምን ይዘን ስናልፍ አክሱም ገብቶ ወጣቶች በጅምላ ሲረሽን ጸብ ተፋፍሟል።
ዓድዋን ይዘን ስናልፍ ዓድዋ ሄዶ ፋብሪካዎች ሲፈታ፣ ሲሰርቅ ጸብ ተጋግሏል።
ዓዲግራት ደርሰን የመድኃኒት ፋብሪካውን የሚነቀለውን ነቅለው የማይነቀለውን ሲያፈራሱ ጸቡ ጫፍ ደርሷል።
ግን የኢትዮጵያ መንግስት ያኔ በዚህም፣ በዚያም ለመዋጋት አቅም አልነበረውም። ውስን ኃይል ነበረን፤ ሽሬን ከያዝን በኋላ ያጠቃውን ጠላት እንከተል ነበር እንጅ የያዝነውን ቦታ እያጸናን አንሄድም ነበር።
ይሄ ጉዳይ ለዛሬ ዋጋ የለውም። ለታሪክ ማንሳት የምፈልገው ጉዳይ ግን አክሱም ወጣቶች ሲገደሉ፣ ዓድዋ ሲዘረፍ፣ ዋዲግራት ሲዘረፍ በርካታ ሰዎች ወደ ኤርትራ ልኬያለሁ።
የላኳቸው ሰዎች ገሚሱ አሁን ከኛ ጋር የሉም። ለምሳሌ ክቡር አቶ ገዱ ያኔ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ነበሩ። ከአንዴም ሁለቴ ኤርትራ ልኬያቸዋለሁ። የላኳቸው የትግራይ ህዝቤን አታጎሳቁሉ፣ ሀብቱን አትዝረፉ፣ ጸቡ ከTPLF እንጅ ከትግራይ ህዝብ አይደለም በሚል ነው (ይህን መልዕክት ለኤርትራ እንዲያሳውቁ ማለታቸው ነው)።
አቶ ገዱ አሁን እኛ ጋ የሉም። ግን ክር/ማተብ አላቸው፤ ህሊና አላቸው። ዛሬ ቢደብቁ በታሪክ ውስጥ ይወጣል። ስለምን ጉዳይ እንደተነጋገሩ እሳቸውም ያውቃሉ፤ ሻዕቢያም ያውቃል፤ እኛም እናውቃለን። አሉ አልሞቱም። እሳቸው (ገዱ) Access ይደረጋሉ ሊናገሩ ይችላሉ።
ጉዳዩ በእሳቸው መፈታት ሲያቅተው አቶ ደመቀን ልኬያለሁ። አቶ ደመቀ አሁንም እኛ ጋ የሉም፤ በህይወት ስላሉ ለእምነታቸው ለህሊናቸው ሊጠየቁ ይችላሉ። ለምን ጉዳይ እንደሄዱ ያውቃሉ።
ታስታውሱ ከሆነ መቐለ ልንገባ ትንሽ ሲቀረን የሦስት ቀን ‘አልቲማተም’ ብለን አውጀን ነበር። ብዙው ምስጢሩ አልገባውም።
የቸገረን እኛ ሽሬን ስንለቅ ከኋላ ይገባሉ። አክሱም ስንለቅ ከኋላ ይገባሉ። መቐሌ ስንገባ ደግሞ ገብተው ትልቁን ከተማ Damage ያደርጋሉ ብለን፥ ካሁን በኋላ ከውቅሮ እናልፋለን ብትሉ ወያኔን ትተን ወደእናንተ ነው የምንዞረው በውጊያው ብለን ውቅሮ ላይ የሚጠብቅ ኃይል አስቀምጠን ነው መቐሌ የገባነው።
ይሄ ጸብ ተፋፍሞ ሄዶ የፕሪቶሪያው ስምምነት ሲፈረም ‘ እንዴት TPLF ሳይጠፋ፣ ትግራይ ሳይወድም ፊርማ ይደረጋል ? ‘ በሚል ነው የመጨረሻ ጫፍ የደረሰው ጸቡ። ከዚህ ኃይል ጋር ነው እንግዲህ ያኔ የTPLF ሰዎች ኢትዮጵያን ለማፍረስ እንስራ ያሉት።
የትግራይ ህዝብን የሚጎዳ እና የሚጠቅም ነገር ይሄ መንግስት ነው የሰራው ወይስ TPLF? (ሁሉም TPLF ላይሆን ይችላል፤ አክራሪ TPLF በሚል ይውሰድ) ማነው? የሚለው ዛሬ ብዙ Emotion፣ ብዙ ፕሮፓጋንዳ፣ ብዙ ውሸት ስላለ ነው፤ ነገ ግን ታሪክ ያወጣዋል።
ማንም ሰው እውነትን ለጊዜው መሸፈን እንጅ ከነአካቴው ማጥፋት አይችልም። እኛ መጨረሻ ፕሪቶሪያ ስንፈራረም መቐለ ለመግባት አንድ ቀን ነበር የቀረን፤ አሸንፈናል ጦርነቱን።
ግን መቐለ መግባት ድል አይደለም። ህዝባችንን የማንጠብቅ ከሆነ ተመልሶ ይዘረፋል፣ ይገደላል። ያ ከሚሆን ሰላም ይሻላል። የኛው ህዝብ ነው ከሚጎዳብን ይቅርብን ብለን ነው የወሰነው።
ዛሬ የTPLF አንዳንድ ሰዎች ያላቸውን አቋም ሳይ ምን ያክል ህዝባቸውን እንደሚጠሉ፣ ምን ያክል የህዝባቸው በደል እንዳማያማቸው ነው የሚገባኝ።
እውነተኛው ፈራጅ ስለሚያይ ማንም አያሸንፈንም። TPLF በኤርትራ ወታደር ዘረፋ እንዳይካሄድበት ስንጠብቀው ኖረን አማራ ክልል ሲገባ ያደረገው ነገር ያሳፍራል። ፋብሪካዎች አፍርሷል። ት/ቤት አቃጥሏል። ባንክ ዘርፏል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት መቐለ ነበረ በብቸኝነት፤ TPLFን አባሮ ሻዕቢያን ሳያስገባ። መቐለ አንድ ቤት የፈረሰ አታገኙም።
TPLFስ ቢሆን አማራ ክልል መጥቶ እንደዚያ አይነት ነገር ማድረግ ነገ ለሚቀየር ታሪክ አስፈላጊ ነበር? እንደዚህ ያለው ኢትዮጵያን ያላስቀደመ ለጊዜው ለሚዲያ ጫወታ የሚደረግ የፓለቲካ ስብዕና በዘላቂነት በራሳችን ህዝብ ላይ ጉዳት የሚያመጣ ብቻ ሳይሆን በታሪክ መነጽር ሊጋባው በየነን ዛሬ ታሪክ እንዳነሳቸው በታሪክ ውስጥ ይነሳል ” ብለዋል።