ኢትዮጵያና የነነዌ ጾም
በቀሲስ አስተርአየ ጽጌ
[email protected]
“አንባቢ ይፈጥን ዘንድ ራእዩን ጻፈው፣ በጻላትም ግለጸው፣ ራእዩ በተወሰነለት ጊዜ ይገለጣል፡፡ ወደ ፍጻሜ ለመምጣት ይቸኩላል፣ ውሸት አይደለም፡፡ ቢዝገይም ይመጣል” (ዕንባቆም 2፡2-3)በሚለው ተንተርሰው የቀደሙ አባቶቻችን “የሚሰማም የሚያነብም ባይኖርም፣ ሰሚ ጆሮ ያላቸው አንብበው የሚረዱ ጥቂት ሰወች ስለሚኖሩ ይጻፍ ይነገር” ይላሉ፡፡
ለኢትዮጵያ ሕዝበ ክርስቲያን ያልተከሰተና ያልተነገረ እንግዳ ነገር የለም፡፡ በየዘመናቱ የሚታዩት ሁሉ እንግዳ የሚሆኑትን ላዲሱ ትውልድና ክስተቶችን ለሚያስተናግዱ መሪዎች ነው፡፡ በኢትዮጵያና በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስቲያኖች ላይ የሚከሰቱት መከራወች የአመጣጣቸው መንገድ ይቀያየራል እንጅ የተለመዱ ናቸው፡፡ ስለዚህ ለኢትዮጵያ ሕዝበ ክርስቲያን የሚያስፈልገው ያለፈውን ታሪክ መመርመርና ሊቃውንት አበው በዝክረ ሊቃውንት ቅኔዎቻቸው የተቀኟቸውን ቅኔዎች መፈተሽ እንጅ አዲስ ሕልምም ራእይም አያስፈልግም፡፡
ለሚከሰቱ ነገሮች አዲስ ራዕይ ምልክት የሚሻ ቢኖር “ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል፡፡ከነቢዩ ከዮናስ በቀር ምልክት አይሰጠውም” (ማቴ 12፡39-42) እንዳለው፦ ከዚህ ቀደም የተከሰቱትን ከመመርመርና ቅኔዎችን በጥንቃቄ ከመመልከት ይልቅ ህልምና ራዕይ መሻት ክፉና አመንዝራ ትውልድ መሆን ነው፡፡ ለኛ ብዙ ምልክቶች ተሰጥቶናል፡፡ሊቃውንት አባቶች ነገረ መለኮቱን የተረጎሙበት አንድምታቸውና ዝክረ ነገር ብለው ቀምረው ያስቀመጡልን ቅኔዎቻቸው ዘመን እያሰገሩ የሚከሰቱትን ሁሉ በግልጽ የሚያሳዩ ናቸው፡፡
ከ 8 አመታት በፊት የነነዌን ጾሞ መነሻ በማድረግ ያቀረብኩት ያባቶች አንድምታ ያለፈውን ያስቃኛል፡፡ ባቀረብኩበት ዘመን ይካሄድ የነበረውን አሳይቷል። በዚህ አመት ነነዌ ጾማችን ላይም ካለፉት ዘመናት በተከታታይ ሲካሄድ የነበረው የኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኞችና የአማራ ህዝብ ላይ የተከፈተው ጦርነት ተፋፍሞና ተባብሶ ህዝቡ ከሰማይ በድሮንና በጦር ጀት ከመሬት ደግሞ በከባድ መሳሪያዎች አሳሩን እያየ፣ ጭፍጨፋና እልቂት እየተካሄደበት ነው። ገዳማት፣ ቤተ ክርስቲያኖች፣መስጊዶች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ሀኪም ቤቶችና ሌሎችም የህዝብ ሀብቶች በመንግስት ተብየው እየወደሙና እንደ ገና ዳቦ በእሳት እየጋዩ ነው። ህዝብ በሚከፍለው ግብር የሚተዳዳር ወታደር ለአቅመ ሄዋን ያልደረሱ ልጆችን፣ መነኮሳትን፣ ባለትዳር ሴቶችን እየተደፈረና እያስነወረ ነው። አባቶቻችን የነነዌ ጾም ከብዙ ህይወታችን ጋራ የተሰናሰለች መሆኗን ያሳዩበትን አንድምታ ከ8 አመታት በፊት ቀርቦ ስለነበረ በድጋሚ ቪዲዮውን በመክፈት ተከታተሉት።