Elias Meseret : የህግ አስከባሪ አካላት በቅርቡ በተደጋጋሚ እየፈፀሙት ያለ ትኩረት የሚሻ ነገር ቢኖር ግለሰቦችን በሙስና፣ የህብረተሰቡን እሴት በመበከል… ወዘተ ጠርጥረን በቁጥጥር ስር አዋልን ብለው ህብረተሰቡን ካስፈነጠዙ እና ሙገሳቸውን አፋቸው ላይ ካረጉ በኋላ ተጠርጣሪዎቹን ካለ አንድ ኮሽታ የሚለቁት ነገር ነው።
ለምሳሌ የዛሬ ሁለት ወር ገደማ አንዳንድ የመንግስት ሚድያዎች በሰበር ዜና ጭምር ሲያቀርቡት የነበረው “ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ በመሰወር ወንጀል የተጠረጠሩ የስፖርት አወራራጅ ድርጅት ባለቤቶችና ተባባሪዎቻቸው በቁጥጥር ስር ዋሉ” የሚለውን ዜና እንይ፣ ዛሬ ላይ አንድም ተጠርጣሪ ሳይቀር በምርመራ ምንም ሳይገኝበት ነፃ ሆኗል ተብሏል።
ፎቷቸው እንደ ሌባ በፌስቡክ ተለጥፎ ‘አጭበርባሪ፣ የታባቱ፣ ይሰቀል’ ሲባል የነበረው ሁሉ ዛሬ ላይ ነፃ ሲሆን አንድም የመንግስት ሚድያ አልዘገበውም (ለዝርዝሩ መሠረት ሚድያ ላይ: https://www.meseretmedia.org/p/100-24
በተመሳሳይ ታዋቂ የሚባሉ ቲክቶከሮች በቅርቡ ፎቷቸው እየተለቀቀ ታሰሩ ሲባል ነበር፣ ህዝብም ‘የታባቱ/የታባቷ’ ሲል ነበር፣ አሁን ግን እስራቸው እንጂ መፈታታቸው ለህዝብ ሳይነገር ሁሉም ተለቀው ስራቸውን ቀጥለዋል። ሌላም፣ ሌላም…
ይህ ምናልባት መታሰራቸው የመንግስትን ጥንካሬ፣ መፈታታቸው ደግሞ ድክመትን ያሳያል በሚል የተፈፀመ እንደሚሆን ልምምዶች አሉ። ነገር ግን ይህ የተጠያቂነት ግርግርን (performance of accountability) እንጂ ተጠያቂነትን ራሱን (accountability) አያመጣም።
ሰው ተጠርጥሮ አይያዝም አይባልም፣ ነገር ሁሉም ሊጠይቅ የሚገባው ነገር ቢኖር:
– ህዝቡ ግለሰቦች ሲታሰሩ ብቻ ሳይሆን ሲፈቱ የማወቅ መብት የለውም?
– እነዚህ ዜጎች በምን ጉዳይ ታሰሩ፣ ምን ክስ በየትኛው አንቀፅ ተመሰረተባቸው? ካልተመሰረተስ ለምን?
– ክስ ሲቋረጥ ወይም እንዲለቀቁ ሲደረግ ማን ውሳኔውን ሰጠ? ባለስልጣናት፣ ፍርድ ቤት ወይስ አቃቤ ህግ ክሱን አነሳ?
– እንዴት፣ በምን ምክንያት እና አግባብ ተፈቱ?
– በጥርጣሬ ታስረው የነበሩት ምን ተሰማቸው? በአደባባይ የጠለሸውን ስም እና ክብራቸውን ምን ማካካሻ ማግኘት ይችላሉ?
ዛሬ ላይ ህዝብ ከመንገድ ላይ በዘፈቀደ እየተያዘ እና እስር ቤት እየገባ ገንዘብ ከፍሎ ይወጣል፣ ስለዚህ ሁሉም ይህን ጥያቄ አሁን ካልጠየ ‘እኔንም ድገሙኝ’ መሆኑ አይቀርም።