ወልቃይት ቀጠና በማይ-ዳጉሻ በኩል የተጀመረው ውጊያ አድማሱን አስፍቶ በምስራቅ ጠለምት እና በምዕራብ ጠለምት ከባድ ውጊያ እየተካሄደ ይገኛል።

ብልፅግና ወልቃይት ላይ የመዘዘው የመጨረሻ ካርዱ!

ከጥር 18/2018 ዓ/ም ጀምሮ በአማራ ክልል ወልቃይት ቀጠና በማይ-ዳጉሻ በኩል የተጀመረው ውጊያ አድማሱን አስፍቶ በምስራቅ ጠለምት እና በምዕራብ ጠለምት ከባድ ውጊያ እየተካሄደ ይገኛል።

ሦስተኛ ቀኑን ባስቆጠረው ውጊያ በሰላሬ፣ በመቃብር አንበሳ፣ ማይበረና ሰራር የተባሉ አከባቢዎችን ጨምሮ በምጫራ ግንባር በአጠቃላይ በሦስት ግንባሮች በከባድ መሣሪያዎች ታግዞ እየተካሄደ መሆኑን መረብ ሚዲያ ለማረጋገጥ ችሏል።

ብልፅግና፡ በባለቤቱ በአማራ ቁጥጥር ስር የሚገኘውን ወልቃይትን ከሕወሓት ታጣቂዎች የሚከላከል መስሎ ተኩስ ከጀመረ በኋላ፡ እንደለመደው በስልታዊ ማፈግፈግ ስም ወልቃይትን ሙሉ ለሙሉ ለሕወሓት በማስረከብ “ወልቃይትን ከወረራ እንዳልከላከል ፋኖ እንቅፋት ሆኖብኛል” የሚል ካርድ ለመምዘዝ መዘጋጀቱም ታውቋል።

ብልፅግናም ሆነ የብልፅግና ተላላኪው በአዴን የወልቃይት ጉዳይ ጉዳያቸው አይደለም። እነዚ ሁለት ፀረ አማራ ኃይሎች ወልቃይትን የሚፈልጉት ለፖለቲካዊ ትኩሳታቸው ማብረጃ ብቻ ነው።

ወዲህ ደግሞ በአዴን የወልቃይትን አጀንዳ የሚያነሳው ፋኖን እርስ በእርሱ ለመከፋፈልና ከሕዝቡ ጋር የመነጠል ስራ ለመስራት ነው።

እንጂማ በአዴን በየትኛው ጊዜና ሰዓት ነው የፌደራል መንግስቱ እግር አጣቢ ከመሆን ወጥቶ ለሕዝብ አስቦና ተቆርቁሮ የሚያውቀው።

የአማራን እርስት አሳልፈው የሰጡ በአዴኖች፣ ከክልሉ ውጭ ያለው አማራ ውክልና እንዳያገኝ በማድረግ ለዘር ፍጅት የዳረጉት በአዴኖች፣ ለመጣ ለሄደው የፌደራል መንግስት ዘዋሪ ቡድን ማጎብደድና መላላክ የማይሰለቻቸው በአዴኖች፣ የፌደራል መንግስቱ ከድሮንና ጄት ጀምሮ በአለም አቀፍ የጦር ሕግ የተከለከሉ መርዛማ መሳሪያዎችን ጭምር ታጥቆ የክልሉ ሕዝብ ላይ የዘር ጭፍጨፋ እንዲፈፅም የፈቀዱና አሁንም ይሄንን ዘግናኝ ድርጊት እየመሩና እያስተባበሩ የሚገኙት በአዴኖች፣ ሕዝቡ አማራዊ ስነልቦና እንዳይኖረው በአጥንትና ጉልጥምት ቆጠራ ተዘፍቆ፡ በጎጥና በመንደር ተወሽቆ እንዲቀር ለማድረግ ሌት ተቀን የሚታትሩት በአዴኖች ናቸው።

ከአማራ ባሕል ያፈነገጡ፣ አማራዊ ስነ ሰብ ያልተላበሱና ስልብ ስነልቦና ያላቸው፣ መላላክን እና መገረድን እንደክብር የሚቆጥሩት የበአዴን ሰዎች እንዴት አያሌ መስዋዕትነት ስለተከፈለበት ወልቃይት ሊያስቡ ይችላሉ?

የበአዴን ሰዎች ከአማራ ተቆርሰው ለተወሰዱ ለየትኛውም እርስቶች እዝነትም ሆነ መቆርቆር ፈጥሮባቸው አያውቅም።እንደውም  ደሴና ኮምቦልቻን ጨምሮ ሙሉ ወሎን በወራሪው ኦህዴድ ጠቅልሎ ለማስወሰድ ጫፍ ደርሰዋል።

ይህ ቡድን ሙሉጊዜውን በግርድና በማሳለፉ አሁን የአማራ ሕዝብ ላለበት ሁኔታ አጋልጦታል።

ይሄው የአማራ ሕዝብ የመከራ ምንጭ የሆነው በአዴን ከፌደራል መንግስቱ ጋር በመመሳጠር ከጥር 18/2018 ዓ/ም ጀምሮ በወልቃይት በኩል አዲስ ጥቃት በመክፈት እንደለመዱት በስልታዊ ማፈግፈግ ስም ገና ነፃነቱን አጣጥሞ ያልጨረሰውን የወልቃይት አማራን ሕዝብ ዳግም ለወረራ ሊዳርጉት ቋምጠው ተነስተዋል።

ቡድኑ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ለመምታት ያስችለው ዘንድ፡ ከርስት በላይ የሆነውን የወልቃይትን ጉዳይ በመግፋት ሕዝቡን ለጥቃት ከመዳረጉም በላይ የፋኖን ኃይል ለማዳከምና እርሱ በእርሱ ለመከፋፈል “ፋኖ ከሕወሓት ጋር ተባብሮ” ወልቃይትን አስወረረብን የሚል አጀንዳ መምዘዙ እጅግ አስገራሚ ያደርገዋል።

ብልፅግና በወልቃይት ጥቃት እንዲመጀመር ማስደረጉ ዋነኛ ምክኒያት ከሰሞኑ የአማራ ፋኖ ወጥ የሆነ አደረጃጀት መመስረቱን ተከትሎ የፈጠረበት ከባድ ድንጋጤና ጭንቀት ነው።

የፋኖን የወደፊት አቅጣጫ ያዛባልናል ብለው ካሰቡት አንዱ የወልቃይትን ጉዳይ አጀንዳ በማድረግና ዳግም በማስወረር፡ አስወረርከን የሚል አማራ ከተነሳም፡ የሕወሓት ታጣቂዎችን ከወልቃይት እንዳላስወጣ ፋኖ እንቅፋት ሆኖብኛል የሚል ካርድ ለመምዘዝ አልሞ ነው።

ነውረኛውና ልፍስፍሱ ብልፅግና የሕወሓት ታጣቂዎች በወልቃይት የከፈቱትን ወረራ ለመቀልበስ መከላከያ ሰራዊቱን ካሰማራው ፋኖ ቀጥታ ያለከልካይ ወደ አራት ኪሎ ያመራብኛል የሚል የቂል መልስ እንደሚሰጥም ይጠበቃል።

ለዛም ነው ብልፅግና በወልቃይት ጥቃት መከፈቱን ተከትሎ አፀፋዊ ምላሽ ወሰድኩ የሚል የተለመደ ቀደዳውን በአክቲቪስቶቹ በኩል እያስነገር የሚገኘው።

ነገ ደግሞ “ስልታዊ” ብሎ የሚጠራውን የማፈግፈግ አይነት ያፈገፍግና ለምን የሚል ጥያቄ ሲነሳበት ወልቃይት ላይ የተቃጣውን ወረራ እንዳልመክት ፋኖ እንቅፋት ፈጠረብኝ በሚል የለቅሶ ፖለቲካ ለመስራት ካሁኑ ድንኳን ተከላ ጀምሯል።

ግራም ነፈሰ ቀኝ፣ ጣፈጠም መረረም የአማራ ፋኖ እያደረገ ባለው የሕልውና ትግል ቀዳሚ አላማው የተከበረ፣ እርስቶቹ የተጠበቁለትና ማንነቱ የማያስጠቃው አማራ እንዲኖር ማድረግ፣ ሕልቆ መሣፍርት ግፍና መከራን ጨምሮ የዘር ጭፍጨፋ ለተፈፀመበት የአማራ ሕዝብ ፍትሕ ርትዕ ማስፈን መሆኑን ሀገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ሐቅ ነው።