እኔ አርጅቻለውኝ ፤መሄጃዬም ደርሷል አንተ ቤት ሠርተህ ህዝቤን ጠብቅ ( የሐመሩ ባለአባት ለሊቀ ጳጳስ ብፁዑ አቡነ ዕንባቆም )

የእኛ አምላክ ባርጆ ነው። የአንተ አምላክ ከባርጆ ከበለጠ ነገ ዝናብ እንዲያዘንብ ንገረው።…ሐመሮች ሊቀጳጳሱ የፈተኑበት ጥያቄ
***

በአንድ ወቅት የቀድሞው የሰሜን ኦሞ [ደቡብ ኦሞ ፣ጋሞ ጎፋ፣ዳውሮ፣ወላይታ] ሀገረሰብከት ሊቀ ጳጳስ የነበሩት እና አሁን በዕረፍት ሥጋ የተገቱት ሊቀ ጳጳስ ብፁዑ አቡነ ዕንባቆብ ለሐዋርያዊ አገልግሎት ወደ ደቡብ ኦሞ ዞን የአርብቶ አደሮች ምድር ወደ ሆነችው የሐመሮች መንደር ይሄዳሉ።

ክላሽ ታጥቀው፤መፋቂያ ጥርሳቸው ላይ ሰክተው ለአፍረተ ስጋቸው ብቻ ብጣሽ ጨርቅ ገላቸው ላይ ጥለው በእዛ ሐሩር በሚያቀልጥበት በረሐ እራቁታቸውን የሚሄዱ የሐመር አርብቶ አደር ወጣቶቸው ጥቁር ቀሚስ ከጥቁር አስኬማ ጋር አድርገው ዱላ [በትረ ሙሴ] የያዙትን አረጋዊውን ሊቀ ጳጳስ እንደ ልዩ ፍጥረት በአግራሞት ያያሉ።

በሐመሮች መንደር ” ለሐዋርያዊ አገልግሎት መጥቻለው” ተብሎ ዝም ብሎ በድፍረት ወንጌል መስበክ አይቻልም። ምን አልባትም በድፍረት አደርጋለው ከተባለ ህይወትን የሚያስገብር ታላቅ ሞት ጠሪ ድፍረት ይሆናል።

ለምንም ዓይነት መንግስታዊም ሆነ ሃይማኖታዊ ተግባር ቅድሚያ የሐመሮችን የማኅበረሰቡን መሪ የሆኑትን በዕድሜ የጎለመሱት አባትን ፍቃድና ይሁንታ ማግኘት ግዴታ ብቻ ሳይሆን ቋሚ አሰራርም ጭምር ነው።

ሊቀ ጳጳሱም ለወንጌል አገልግሎት ፍቃድ ለማግኘት የሐመሮችን ባለአባት ለማግኘት ወደ ሐመሮች የጎሣ መሪ እልፍኝ ውስጥ ከአስተርጓሚያቸው ጋር ገቡ።

የሐመር ባለአባትም ጥቁር በጥቁር ሆነው የመጡትን ሊቀ ጳጳስ ተመለከቱ። ለተከበረ ሰው የሚቀርበውን የቁርበት ምንጣፍ አስወጥተው እንዲነጠፍላቸው አስደረጉ። በተነጠፈውም ቁርበት ላይ ሊቀ ጳጳሱ እንዲቀመጥ አዘዙ።

ሊቀ ጳጳሱ የመጡበትን ጉዳይ ለሐመር ባለአባት አስረዱ፤”የሐመር አባላትን ጥምቀት አስጠምቀው ኦርቶዶክስ ለማድረግ እንደሚፈልጉ እና እግዚአብሔር የሚባል አምላክን እንዲቀበሉ” በግልጽ ተናገሩ።

የሐመር ባለአባትም ለረጅም ሰዓት በዝምታ ሆነው ሊቀጳጳሱኑን ሰሙ። በስተመጨረሻም አንድ ቃል ከአንደበታቸው አወጡ።

……”ዝናብ ከዘነበ ሣር ይበቅላል። ሣር ካለ ከብት ሣሩን ይመገባል። ከብት ካለ ወተት እና ሥጋ አለ። ወተት እና ሥጋ ካለ ደግሞ ሰው ይኖራል።ርሃብ አይኖርም ። ደስታ ብቻ ።ስለዚህ የእኛ አምላክ ባርጆ ነው። እስከዛሬ ዝናብ እያዘነበ ከብቶቻችንን የሚያኖረው እሱ የእኛ አምላክ ነው።አሁን ላይ ግን ለብዙ ወራት ዝናብ ጠፍቷል።ባርጆ ተጣልቶናል መሠለኝ። ከብቶቻችንን ይዘን ሣር ፍለጋ እየተንከራተትን ነው።ባርጆ ተጣልቶናል። ነገር ግን የአንተ አምላክ ከባርጆ የሚበልጥ ከሆነ ነገ ዝንብ እንዲያዘንብ ንገረው።” ሲሉ የጎሳው መሪ ሊቀ ጳጳሱን አጣብቂኝ ውስጥ የሚከት የብቃት ፈተና ውስጥ አስገቧቸው።

ሊቀጳጳሱም ግራ ተጋቡ። አንቀጽ ጠቅሰው ስለትዕግስትና ስለእምነት እንዳይሞጉቱ ሐመሮች አምላክን ቀጥታ በተራዳኢነት በመጋቦቱ እና በታምራቱ የመመልከት ልምድ አላቸው እና በጣም ፈሩ።

በስተመጨረሻም ሊቀ ጳጳሱ ከሐመሮች መንደር ሲወጡ ግን አንድ ቃል ብቻ ለአምላካቸው በአርምሞ ተናገሩ።….. ቅድስት ሥላሴ ሆይ…ሰማይን አዝዤው ዝናብ እንዳላዘንብ ኤልያስ አይደለሁም፣ቃል አውጥቼ ደመናንን እንዳላዝ ደካማ ነኝ ታውቃለህ። ይህ ህዝብ ርስትህ እንዲሆን እና ስምህ በእዚህ ምድር እንዲከብር ፍቃድህ ከሆነ እኔን ሳትመለከት ነገ ዝናብ ስጣቸው። ከመከራ ሰውራቸው ። ታምርህን ገልጠህ ህዝብህን አድን”

የወንጌል አንቀጽ ተጠቅሶ፤መጸሐፍት ተዘርግቶ ማስተማር የማይቻልበት ማህበረሰብ ውስጥ በምንም ነገር ወንጌልን ማስረዳት እንደማይቻል ያወቁት ሊቀ ጳጳሱ እግዚአብሔር ይህን ህዝብ ከወደደ ዝናብ አዝንቦ ለቤቱ እንዲጠራቸው ብቻ የሰማይ መስኮትን ይከፈት ዘንድ ብቻ ጠበቁ።

የእግዚአብሔር መልካም ፍቃድ ሆነ። በነጋታው ምድርን የሚያረሰርስ በእዛ መንደር ዘንቦ በማያውቅ ልክ ዶፍ ዝናብ ዘነብ ።አንድ ቀን ሁለት ቀን እያሉ ተከታታይ የዝናብ ወቅት ሆነ።የሐመሮች የወራት ድርቅ አበቃ። የሐመሩም ባለአባት እጅግኑ ተደነቁ።

በፍጥነትም ሊቀጳጳሱን ጠርተው አመሰገኑ። ያማረውን ፈሪዳ አረዱ። ህዝቡን የደስታ ምሽት እንዲያከብር አዘዙ። የሊቀ ጳጳሱን በጭፈራ ተቀበሉ።

የሐመሮች በለአባት የማይታይ፣መጨረሻው የቱ ጋ እንደሆነ የማይታወቅ ሰፊ ባዶ ቦታ በጣታቸው እያመላከቱ …”እኔ አርጅቻለውኝ ፤መሄጃዬም ደርሷል። አንተ ቤት ሠርተህ ህዝቤን ጠብቅ”… ሲሉ ትንቢት የሚመስል ቃል የአደራ ቃል ለሊቀ ጳጳሱ አሳሳቡ።

ቤተክርስቲያንም በሐመሮች መንደር በአጭር ጊዜ ውስጥ ተሠራ።ሐመሮችም መጥተው እንዲጠመቁ በሐመር ባለአባት በኩል የግዴታ አዋጅ ታወጀ።

የባለአባታቸውን ድምጽ የሰሙ ሐመሮች ከብታቸውን ትተው ወደ መቅደስ መጥተው የካህናት መዳፍ እስኪዝል ድረስ ተጠመቁ።

እልፍ ነፍሳት ዳኑ። በአጭር ቀናት ውስጥ ሐመር ኦርቶዶክሳዊ ምድር ሆነች። የሐመሩም ባለአባት ህዝቤን ጠብቅ ብሎ ለሊቀጳጳሱ በነገሩት ትንቢት ከሚመስል ቃላቸው በኃላ ስርዓተ ጥምቀት ከተፈፅሞላቸው ቀናትን ቆይተው ይህችን ዓለም ተሰናበቱ፣ ከካራን ወጥተው ከነዓንን ወረሱ።

ትላንት በእዚህ መልኩ ሐመር ላይ የተጀመረው ሐዋርያዊ አገልግሎት ዛሬ ከ90% በላይ ሐመሮችን ኦርቶዶክስ ማድረግ ተችሏል። የሐመር ልጅ የሆኑ ዲያቆናት እና ካህናትን ፈርተዋል።

በሙሴ ጸሊም፣አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ እና አቡነ ዜና ማርቆስ ስም የደቡብ ኢትዮጵያ ግዙፉ ገዳም ተገደመባቸው። ይህ የወንጌል እሳት በደቡብ ኦሞ ዛሬም ተቀጣጥሎ በዓመት እስከ 50ሺህ አርብቶአደሮች ሐብተ ወልድ ስመ ክርስትና ማግኘት ችለዋል።

ዛሬ ወደ ሐመር የሚሄድ ቱሪስት ኢቫንጋዲን ብቻ ተመልክቶ ሳይሆን የሚመለሰው ታላላቅ ገዳማትንም ተሳልሞ በረከት ያፍሳል።ቅድስ ቤተክርስቲያን ሐመር ላይ ተቃዋሚዎቿን ዘርራ፣የሚፃረሯትን ጥላ በአሸናፊነት ተሰይማለች።

ያ የሐመሯ ቆንጆ ተብሎላቸው የተዘፈነላቸው ነፍሳት ዛሬ አኮቴት ለአምላካቸው የሚያቀርቡ የተወደደ ንጉስ ልጅ ሆነዋል።ከቡስካ በስተጀርባ ብሎ ፍቅረ ማርቆስ ደስታ የተረከላቸው ህዝብ ቡስካን በዝማሬ ቀድሰው፣ተራራቸው ላይ ገዳም ገድመዋል ቅዱስ መስቀሉ የባህል ልብሳቸው አካል ሆኖ እምነት እና ውበታቸውን ይገልጣል።

አማናዊ ታምር ማለት ይህ ነው። እንደ ቃና ዘገሊላ አምላክ ሰዎች ያምኑበት ዘንድ ታምራቱን የገለጠበት መዳንን የሚያጸና ሰው ማጥመጃ ታምር።

ወደ ሐመር ስትሄዱ ኢቫንጋዲ ብቻ ሳይሆን በዲመካ በስተ ምዕራብ የተተከለውን አቡነ ሙሴ ጸሊም፣ኦሞራቴ አከባቢ የተተከለውን ዜና ማርቆስ ገዳም ብትሳለሙ ድጋሚ ሐመርን ስታስቡ መንፈሣዊ ነገር ብቻ በአእምሯቸው እንዲመላለስ ታደርጋላችሁ።

የብፁዕነታቸው በረከት ይደርብን !!!

እግዚአብሔር ይመስገን !!!