የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ መመስረቱን አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ትብብር ንቅናቄ የተሰጠ መግለጫ

የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ መመስረቱን አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ

የኢትዮጵያ ትብብር ንቅናቄ የፋኖ ኃይሎች ጥር 09፣ 2018 ዓ.ም. የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ በሚል ስያሜ ውህደት መፍጠራቸውን በማበሰራቸው የተሰማውን ጥልቅ ደስታ ይገልጻል።

የአማራ ሕዝብ በጠባብ ብሄረተኞች አገዛዝና አምባገነናዊ የፓለቲካ ስርአቶች ላለፉት 30 ዓመታት ከፍተኛ ግፍና ሰቆቃ የደረሰበት መሆኑን ይታወቃል። ዛሬ ድረስ የአማራ ህዝብ በማንነቱ ሲገደል፣ ሲፈናቀል፣ ሲሳደድ እያየን ነው። ይባስ ብሎ አሁን ያለው የአብይ አህመድ አገዛዝ በግልጽ “ነፍጠኛን ወገቡን ሰብረነዋል ገናም እንሰብረዋልን” በማለት ከመሳለቅና ከመዛት አልፎ ጦርነት አውጆበት፣ የአማራን ምድር የሰቆቃና የመከራ ምድር አድርጎታል። አማራ ከኦሮሞ አካባቢዎች በገፍ ተገድሎአል፣ ንብረቱ በግፍ ተነጥቆአል፣ በብዙ ሺዎች ተፈናቅለዋል። ግማሹ በመጠለያ፣ ግማሹ መጠለያ አልባ እንዲሆን ተደርጓል። የአማራ ሕዝብ በተደጋጋሚ ወደ አዲስ አበባ እንዳይገባ በአብይ አገዛዝ ሲከለከል እንደነበር የማይዘነጋ ነው፣ በኦሮሞ ታጣቂ ኃይሎችም በተደጋጋሚ ጠለፋና ግድያ ተፈጽሞበታል። ይህ ሁሉ አልበቃ ብሎ አማራን ትጥቁንና ቀብቶውንም እናስፈታለን በማለት ባለፈው ሁለት ዓመት ተኩል ወታደር አዝምተውበታል።

ስለሆነም አማራ ህልናውንና ማንነቱን ለማስጠበቅ በፋኖነት እየታገለ ይገኛል። ከዚሁም በመነሳት ንቅናቄያችን የአማራ ሕዝብ ትግል ፍትሃዊ በመሆኑ ሊደገፍ ይገባል ይላል፣ እየደገፈም ይገኛል። የፋኖ ትግል 3 ዓመት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ ሕዝባዊነቱን አረጋግጦአል። በአስደናቂ ፍጥነት ትልቅ ኃይል መስርቶ መንግስትን እያንገዳገደ ይገኛል። ጥሩ ድስፕሊን ያለው፣ የተማረኩ ጠላቶችን ሰብኣዊ በሆነ መንገድ የሚይዝና ሕዝቦችን ለማቀራረብ የሚሰራ መሆኑን ለዓለም
አስመስክሯል። ልዩ ልዩ የአለም አቀፍ ተቋማትና መገናኛ ብዙሃን ይህን ሀቅ ዘግበዋል።

ሌላው የኢትዮጵያ ህዝብም አሁን ካለው ዘረኛና ጨካኝ አምባገነን የአብይ አህመድ አገዛዝ ስርዓት፣ ፋኖ ሊታደገን ይችላል በሚል በተስፋ
እየተጠባበቀ መሆኑን እንገነዘባለን። ፋኖ በዚሁ አጭር ጊዜ አስደናቂ በሆነ ፍጥነት ከትንንሽ ስኳዶችና ኃይሎች ወደ እዞች ድረስ ለመደራጀት ችሏል። ሆኖም አደረጃጀቱ በየቀጠናውና በተለያዩ ኃይሎች ሆኖ ያልተማከለና ያልተቀናጀ በመሆኑ ሊገኝ የነበረውን ጥቅምና እድገት ከመገደቡ በላይ፣ በነዚህ ኃይሎች
መከከል ፉክክርና ግጭት እንዳይፈጠር ስጋት ሆኖ ቆይቶ ነበር። በዚህም ሂደት ጠላት ቀዳዳ ለመፍጠር ያልሞከረው ሴራ፣ ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም። በገንዝብ ለመደለል፣ በድርድር ስም በተናጠል ሽምግልና በመላክና እርስ በርስ እንዲጠራጠሩ ለማድረግ፣ ትንሽ የልዩነ ፍንጭ ሲያገኝ በስፋት በሚድያ ውዥንብር እንዲፈጠር ለማድረግ ሞክርዋል። ሆኖም ጠላት እንደተመኘውና ብዙ ሕዝብ በስጋት ውስጥ የመውደቁን ያህል የተፈራው ሳይሆን፣ ደልዳላ መሰረት እንዳለው ያስመሰከረበት አጋጣሚ ሆኗል። በፋኖዎች ልዩነት ስለተፈጠረ
እየተዳከሙ ነው በሚባለበት ወቅት፣ በሁሉም ቀጠናዎችና እዞች አስደማሚ የሆኑ ድሎችን እየተቀናጁ እንደመጡ አይተናል፣ እያየንም ነው።
ዛሬ ላይ በፋኖ የተመሰረተው ውህድ የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ በንቅናቄያችንና በመላው ትግሉን በሚደግፍ ሕዝብ ላይ የነበረውን
ስጋት ያስወገደ እና በጎ ምኞታችንን እውን ያደረገ፣ ተስፋችንን ያለመለመ በመሆኑ ታላቅ ደስታ ይሰማናል። ይህ ውህደት ትግሉን በሁሉም አቅጣጫ (ወታደራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ) እድገቱን ወደ እንድ እምርታ ያደረገ መሆኑን እናምናለን። ለሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብም ተስፋ እንደሆነና በውስጥም በውጭም የሚገኙ ደጋፊ ኃይሎችም ትግላቸውን እንዲያስተባበሩና እንዲጠናከሩ መንገድ ከፍቷል ብለን እናምናለን።

በመጨርሻም የትግሉ መቋጫ፣ ያለውን ስርዓት አስወግዶ ፍትሓዊና አሳታፊ የሆነ የፓለቲካ ስርዓት መመስረት መሆኑን በመገንዘብ፣ የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ በአጭር ጊዜ የትግሉን ፍኖተ ካርታ በመዘርጋት ሁሉንም ኢትዮጵያውያን በማሳተፍ ሃላፊነቱን ይወጣል ብለን እናምናለን።
ድል ለአማራ ሕዝብ ፍትሃዊ ትግል!
ድል ለተጨቆኑ የኢትዮጵያ ማህበረስቦች ሁሉ!

የኢትዮጵያውያን ትብብር ንቅናቄ!