የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣን፣ ዋዜማ ሬድዮ የአገሪቱን “ሕገ-መንግሥት” እና “የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ” እንዲሁም “መመሪያዎች” እና “የሙያ ስነምግባር” አክብሮ ለመሥራት ፈቃደኛ ባለመኾኑ “የሥራ ፍቃዱን” እና “እውቅናውን” ዛሬ እንዲመልስ አድርጌያለሁ ሲል ዛሬ ማምሻውን ባሠራጨው መረጃ አስታወቀ።
ባለሥልጣኑ የሚዲያው ዘገባዎች የአገሪቱን “ብሔራዊ ጥቅም የሚጻረሩ”፣ “ሚዛናዊነት የሚጎድላቸው”፣ “የፌዴራልና የክልል መንግሥታት አስተያየትና ምላሽ” ያልተካተተባቸው፣ “ሁከት ቀስቃሽ” እና “የአንድ ወገን” ዘገባዎች እንደኾኑ “በክትትል” እና ከዜጎች በደረሱኝ “አስተያየቶች” እና “ጥቆማዎች” አረጋግጫለሁ ብሏል።
ለሚዲያው “ተደጋጋሚ የእርምት ግብረ መልስ” ስሠጥ ቆይቻለሁ ያለው ባለሥልጣኑ፣ ኾኖም ሜዲያው የተሠጠውን “አስተያያት” እና “የማስተከከያ እርምጃ” ባለመቀበሉ ፍቃዱን እንዲመልስ ማድረጉን ገልጧል። ባለሥልጣኑ፣ ለዋዜማ ሬዲዮ ከሁለት ወር በፊት “የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ” ሠጥቶ እንደነበርም ጠቅሷል።
ከዋዜማ አስተዳደር በኩል እስካሁን ይፋዊ ምላሽ አልተሰጠም።