ከ21 የሚበልጥ የአፍሪካ ስደተኞች አስክሬን በጅምላ መቃብር በሊቢያ መገኘቱ ተነገረ።
በምስራቃዊ ሊቢያ በሚገኝ አካባቢ ከ21 በላይ የሚሆን የስደተኞች አስክሬን በጅምላ መቃብሬ መገኘቱን የጸጥታ ኃይሎች ገልጸዋል።
አጅዳቢያ በተባለ አካባቢ ከሰሃራ በታች ካለው አፍሪካ የመጡ ስደተኞችን ተይዘው እንደሚገኙ የጸጥታ ኃይሎች ሪፖርት ከደረሳቸው በኋላ ወደ አካባቢው አምርተው በእርሻ አካባቢ የጅምላ መቃብሩን ማግኘታቸው ሲነገር ተይዘው ስቃይ ሲፈፀምባቸው የነበሩ 10 ሰዎችም ተለቀዋል ተብሏል።
ስደተኞቹ ተይዘው ገንዘብ ከተጠየቀባቸው በኋላ ቤተሰቦቻቸው የተጠየቀውን ገንዘብ ባለመክፈላቸው ነው የተገደሉት ሲሉ አስተዳዳሪዎች ገልጸዋል።
የእርሻ ስፍራው ባለቤት በቁጥጥር ስር መዋሉና የእርሻ ስፍራው ላይ የጅምላ መቃብር እንደነበር ማመኑ ሲነገር ተጨማሪ ምርመራዎች ይቀጥላሉ ተብሏል።
በተመድ መረጃ መሰረት ሊቢያ ከ44 ሃገራት የተውጣጡ ከ900ሺህ በላይ ስደተኞች የሚገኙባት ስትሆን በተደጋጋሚ በተለያዩ ቡድኖች ስደተኞች እየተያዙ ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚጠየቅባቸውና እንደሚገደሉ ይታወቃል።
ዘገባው የሮይተርስና የዶይቼ ቬለ ነው።