አገዛዙ በውጊያ የተገደሉ የራሱ ወታደሮችን አስከሬን በድሮን ደበደበ!

አገዛዙ በውጊያ የተገደሉ የራሱ ወታደሮችን አስከሬን በድሮን ደበደበ!

በምስራቅ ዐምሓራ ቀጠና ከወልድያ ከተማ ዙሪያ አከባቢዎች ጀምሮ እስከ ቃሊምና ቃሊም ዙሪያ አከባቢዎች ድረስ በተደረገው ተጋድሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአገዛዙ ወታደሮች ሙትና ቁስለኛ መደረጋቸውን ለማረጋገጥ ተችሏል።

ውጊያው የተካሄደው ጥር 05/2018 ዓ/ም ማለዳ ጀምሮ እስከ ምሽት ድረስ ሲሆን፡ ከ13 ሰዓታት በላይ የጨበጣ ትንቅንቅ ነው የተደረገው።

በአፋብኃ ምኒልክ ዕዝ ከሀውጃኖ ክ/ጦር እና ከጄነራል አሣምነው ፅጌ ክ/ጦር የተወጣጡ የፋኖ አሃዶች ጥር 05/2018 ዓ/ም ማለዳ ጀምሮ፡ ከወልድያ ዙሪያ ማለትም ጥቁር ውሃ ምላሽን ይዞ እስከ ቃሊም ድረስ በወሰዱት ውጤታማ ነው በተባለ የመከላከልና የመልሶ ማጥቃት እርምጃ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአገዛዙ ወታደሮችን በመደምሰስና በርካታ ክላሽንኮቭ መሣሪያ ከነ ተተኳሹ በመማረክ ድል መቀዳጀታቸውን መዘገቡ አይዘነጋም።

ያለምንም ማቋረጥ ለተከታታይ 13 ሰዓታት በተደረገው የጨበጣ ውጊያ፡ ከወልድያ ከተማ ዙሪያ ሚጦና ጃርሳን ጨምሮ ከጥቁር ውሃ ምላሽ ጀምሮ አላገዶ፡ አፍሪኬር፡ ቃሊም መገንጠያ፡ ዘንዶ ጅራት(ከሳምት በፊት የአየር መቃዎሚያ እስከ ኦራሉ የወደመበት ቦታ)፣ ቃሊም መገንጠያና ቃሊም ድረስ የሸፈነ ተጋድሎ ተደርጓል።

አገዛዙ ሁለት ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ጨምሮ በወልድያ ሼይኽ መሐመድ ሁሴን አል አሙዲን ስታዲየም እና በከተማዋ ኢንዱስትሪ መንደር ተብሎ በሚጠራው አከባቢ ባጠመደው ጄነራል መድፍ እንዲሁም በከተማዋ አዲሱ ማረሚያ ቤት እየተሰራ በሚገኝበት ጉቦ ተብሎ በሚጠራው አከባቢ ባጠመደው ሞርተር፣ ቢኤምና ዙ23 ታግዞ ከሁለት ዕዝ የተወጣጡ ከሦስት ክፍለጦር በላይ ወታደሮችን በሚኒሻና አድማ ብተና መንገድ መሪነት በማሰለፍ ሲዋጋ የዋለ ቢሆንም፡ ነገር ግን ይህ ሁሉ ግትልትል ኃይል የፋኖን ጥቃት መቋቋም አቅቶት ከባድ የሆነ የሰብአዊና ቁሣዊ ኪሳራን በመከናነብ “ሺ ፈሳም አንድ ጎማ አይነፋም” ሆኖ ቀርቷል።

በምኒልክ ዕዝ ስር ከሀውጃኖ ክ/ጦር እና ከጄነራል አሣምነው ፅጌ ክ/ጦር የተወጣጡ የፋኖ አሃዶች በወሰዱት ስኬታማ በሆነ የመከላከልና የመልሶ ማጥቃት እርምጃ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአገዛዙ ወታደሮችን መደምሰስ ችለዋል።

የጠላት ኃይል በሚደመሰሱበት ወታደሮች ልክ ተጨማሪ ኃይል እያስገባ የዋለ ሲሆን፡ ምሽት ላይ ግን  የሚጨምረውን ኃይል በማቆም ሁለት ሰው አልባ አውሮፕላኖች በማሰማራት ተከታታይ የዘፈቀደ ድብደባዎችን ፈፅሟል።

በዚህም በሰዓታት ልዩነት ከ12 ጊዜ በላይ የድሮን ጥቃት የተፈፀመ ሲሆን፡ አገዛዙ የእሱን ስልጣን ለማራዘም ሲሉ ሲዋጉ በፋኖ የተገደሉ የመከላከያ ሰራዊት አባላትን አ*ስ*ከ*ሬ*ን ደብድቧል።

ይህም፡ የፋኖ አባላቱ በውጊያው ከተገደሉ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ ክላሽና ሌሎች ወታደራዊ ንብረቶችን እንዳይሰበስቡበት በማሰብ የፈፀመው ዘግናኝ ድርጊት ነው ሲሉ ወታደራዊ ምንጮች ገልፀዋል።

በድሮን ጥቃቱ በፋኖ በኩል የደረሰ ጉዳት ባይኖርም ነገር ግን በቤታቸው ውስጥ የነበሩ ንፁኋኖች ተገድለዋል።

በጥቃቱ ከተገደሉ ንፁኋኖች መካከል አንድ የቤተክርስቲያን ጠባቂ አባትን ጨምሮ ሌሎች በቤታቸው ውስጥ የነበሩ ሴትና ህፃናት እንደሚገኙበት ታውቋል።

በተጨማሪም ከወልድያ ከተማ በሚወነጨፍ መድፍ ሕይወታቸው ያለፈና የቆሰሉ ንፁኋኖች መኖራቸው የተነገረ ሲሆን፡ የመድፍ ጥቃቱ የቤት እንስሳቶችንና ተሰብስቦ የተከመረ የማሽላና የጤፍ ነዶ ማውደሙን የምስራቅ ዐምሓራ ዘጋቢዎች ለማረጋገጥ ችለዋል።