“በ10 እና በ15 ደቂቃ ውስጥ ሱቅና መኖሪያ ቤት እንዴት ሆኖ ነው የሚደመሰሰው? ምን ማለት እንደሆነ አልገባኝም” – እንባ የሚተናነቃቸው እናት
በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ 4 ነዋሪ ከነቤተሰባቸው የሚኖሩበት “50 ዓመት የኖሩበት የይዞታ” ቤታቸው፣ “‘ዛሬ 8 ሰዓት ሊፈርስ ነው’ ተባልኩ” ሲሉ ቅሬታቸውን በቲክቫህ ኢትዮጵያ በኩል ገልጸዋል።
ምን አሉ? “ከዚህ በፊት መጥተው በ13.5 ለክተው ነበር ቦታውን። አሁን እንደገና ትናንት መጥተው ሙሉ ቤቱን ለኩት። ሱቅ፤ መኖሪያ ቤት አለ። ሁለቱንም የያዘ ነው ግቢው። ከዚያ በኋላ ‘በሙሉ ነው የሚፈርሰው’ ብለው እያንዳንዱን ቤቱን ለኩት።
እንዴት ይሆናል? ልኬት አውጥታችኋል፤ ለመንገድ ልማት 13.5 ለክታችኋል እሱን ተቀብለናል ብዬ ስላቸው ‘ለመንገዱ ርዝመት ነው እንጅ ልኬት አይደለም’ አሉኝ። ምንም መናገር አልቻልኩም ለዛ ነው ብዬ ዝም አልኩ።
እንዳለ ሙሉውን ቤት እያንዳንዱን ለክተው ጨርሰው ዛሬ ጠዋት መጥተው ‘እቃችሁን አውጡ ዛሬ እናፈርሳለን’ አሉ።
የ95 አመት እናት አለችኝ። ሱቁ መተዳደሪያችን ነው። ቤቱ መኖሪችን ነው። ሙሉ ንብረታችን ያለበት ቤት ነው። በ10 እና በ15 ደቂቃ ውስጥ ሱቅና መኖሪያ ቤት እንዴት ሆኖ ነው የሚደመሰሰው? ምን ማለት እንደሆነ አልገባኝም።
እኛእኮ ልማቱን እንቀበላለን፤ ተቀብለናልም። ይልማ። ሀገራችን እንድትለማ ነው የምንፈልገው። ግን አግባብ ባለው መንገድ እኛም ሳንጎዳ፣ ብዙ ነገር ተነጋግረን መፈረም ያለብንንም ፈርመን መሆን አለበት። ያለወረቀት/ደብዳቤ ሜዳ ላይ መጥተው ለምንድን ነው እንዲህ የሚያደርጉት?” ብለዋል።
እኝሁ እናት ይህን ያደረጉት እነማን እንሆኑና ህጋዊ ደብዳቤ ይዘው እንደሆን ስንጠይቃቸውም፣ “ምንም ነገር የለም። ከወረዳ 4 ነው የመጣነው፤ ከቦሌ ክፍለ ከተማ ነው የመጣነው’ ነው የሚሉት። ከአትላስ ጀምሮ እያፈረሱ፤ ‘8 ሰዓት እናንተ ጋር እንደርሳለን፤ እስከዛ እቃችሁን አውጡ’ ብለው ሄዱ” ሲሉ ተናግረዋል።
“ለመንገድ ልማት እሺ ብለን ተቀብለን ለክተዋል። መስመር አድርገው ነው የሄዱት። አሁን ሙሉውን ሱቁንም መኖሪያ ቤቱንም እንዳለ ደምስሳችሁ ባዶ እንዲሆን ነው የምንፈልገው አሉ” ብለው፣ “እቃችንን፣ ንብረታችንንስ የት ወስደን እንጣለው? አስፓልት ላይ እናስቀምጠው አውጥተን? ግራ ነው የገባን። ምንድን ነው እንዲህ አይነት ነገር?” ሲሉ ጠይቀዋል።
ልዩ ቦታውን ስንጠይቃቸው፣ “በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 አዲስ አለማየሁ ትምህርት ቤት ፊት ለፊት በእምነት መድኃኒት ቤት ከሚለው ጀምሮ እስከ ሱቁ ድረስ ነው የኔ ቤት” ብለው፣ ቪዲዮም ቀርጸው ልከዋል።
“ቤቱ የግል ይዞታችን፤ ንብረታችን ነው። ወደ 50 ዓመት የተኖረበት ቤት ነው” ያሉት እኝሁ እናት፣ “ልማቱን ተቃዋሚ አይደለሁም፤ ግን በትክክለኛ በህጉ መንገድ መፍረስ ያለበት ይፈርሳል ለመንገድ፤ የቀረውን ደግሞ ማልማት ያለብኝን መንግስት በሰጠኝ ዲዛይን ማልማት እችላለሁ። ከዚህ በፊት ተጠይቅ አላውቅም” ብለዋል።
ወደ ቦሌ ክ/ክፍለ ያደረግነው ሙከራ ለጊዜው ያልተሳካ ሲሆን፣ አመራሮቹን የመጠየቅ ሙከራው ይቀጥላል።