በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ፣ በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ሁሉም ወገኖች ከፖለቲካ በላይ ሕዝብን እንዲያስቀድሙ እና ሕዝቡ የወደፊት የፖለቲካ ሕይወቱን በትክክለኛው ጊዜ እንዲወስን እድል እንዲሠጡ ጠየቁ።
አምባሳደር ማሲንጋ ይህን ጥሪ ያቀረቡት፣ ዛሬ በአማራ ክልላዊ መንግሥት ሥር በጊዜያዊነት በተቋቋመው የወልቃይት-ጠገዴ-ሁመራ ዞን ጉብኝት ካደረጉ በኋላ ባስተላለፉት መልዕክት ነው። አምባሳደሩ፣ እያንዳንዱ ዜጋ “ደኅንነቱን” እና “ሰብዓዊ ክብሩን” በሚያስጠብቅ ሁኔታ ሕይወቱን የት ቦታ ላይ መመስረት እንዳለበት “ኢትዮጵያ-መር” በሆነ እና “የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሚደግፈው” ማዕቀፍ መሠረት የሚወስንበትን ሂደት አሜሪካ ትደግፋለች ብለዋል።
በርግጥ ይህን ተፈጻሚ ማድረግ “ውስብስብ” መሆኑን እንረዳለን ያሉት ማሲንጋ፣ ሆኖም በግጭቱ ጉዳት ለደረሠባቸው ወገኖች ደኅንነት ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋል ሲሉ በመልዕክታቸው አጽንዖት ሠጥተዋል። የተጎዱ መሠረተ ልማቶች፣ የሕክምና እና ሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎቶች እጥረትን ጨምሮ የአካባቢው ሕዝብ ያሉበትን ችግሮች በአካል መመልከታቸውንም አምባሳደሩ ገልጸዋል።
በግጭቱ የተፈናቀሉ ሰዎች በዓለማቀፍ እርዳታ ላይ ተንጠልጥለው እንደቆዩ ማሲንጋ የጠቀሱ ሲሆን፣ ሰብዓዊ እርዳታ ግን “ዘላቂ መፍትሄ” ሊሆን አይችልም ብለዋል።