በኢራን ለሁለት ሳምንታት ለሚጠጋ ጊዜ የቀጠለውን አገር አቀፍ ተቃውሞ ተከትሎ፣ የሟቾች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን አንድ የኢራን ባለሥልጣን ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ ማረጋገጣቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
በዚህም እስካሁን በደረሰው ግጭትና የኃይል እርምጃ ቢያንስ 2,000 ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸው ሲነገር፤ የጉዳቱ መጠን እጅግ የከፋ መሆኑንም ያሳየ ነው ተብሏል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሰልፈኞች እያደረጉት ያለውን ተቃውሞ አጠናክረው እንዲቀጥሉ የሚያበረታታ መልዕክት አስተላልፈዋል።
“እርዳታ በመንገድ ላይ ነው” ሲሉ ቃል የገለጹት ፕረዚዳንቱ፥ ይህም አሜሪካ በቀጣይ ቀናት ለኢራን ሕዝብ ድጋፍ የሚሆኑ ተግባራዊ እርምጃዎችን ልትወስድ እንደምትችል ፍንጭ የሰጠ ሆኗል።
የተቃውሞው ምክንያት ምንድን ነው?
በተለያዩ ማዕቀቦች የተነሳ ኢኮኖሚዋ የተዳከመው ኢራን በፈረንጆቹ ታህሳስ 28 የመገበያያ ገንዘቧ ሪያል በመውደቅ አንድ የአሜሪካ ዶላር በ1.4 ሚሊየን ሪያል መመንዘሩን ተከትሎ ተቃውሞው ተቀስቅሷል።
ተቃውሞው በአንድ ለሊት የዘይትና የሌሎች አስፈላጊ ምርቶች ዋጋ በእጥፍ በመጨመሩ ሲቀሰቀስ መጀመሪያ በሱቅ ባለቤቶች መነሳቱና ቀስ በቀስ ተማሪዎችን ጨምሮ ወደሌሎች የህብረተሰቡ አካላት ተስፋፍቷል።
የሃገሪቱ የማዕከላዊ ባንክም ለአንዳንድ አስመጪዎችን ዶላር በርካሽ ይሰጥበት የነበረውን አሰራር አስቀርቷል።
የኢራን ምላሽ
የኢራን መንፈሳዊ መሪ አያቶላህ አሊ ሆሚኒ ተቃዋሚዎች የአሜሪካውን ፕሬዚዳንት ለማስደሰት ነው ተቃውሞ የወጡት ብለው ተቃውሞውን አጣጥለውታል።
ተቃዋሚዎች የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ እንዲፈርስ መጠየቃቸውን ተከትሎም መንፈሳዊ መሪው እስላማዊ ሪፐብሊኩ በደም የመጣ በመሆኑ ወደኋላ አይመለስም ሲሉ ተደምጠዋል።
የእስላማዊ ሪፐብሊኩ በ1979 ሲመሰረት የኢራን የመጨረሻው ሸሃ (ንጉስ) ልጅ ልዑል ረዛ ፓህላቪ ተሰደው በአሜሪካ የሚገኙ ሲሆን፣ ትራምፕ የኢራን ህዝብን ለመርዳት ጣልቃ ለመግባት እንዲዘጋጁ ጠይቀዋል።
በኢራን ለመጨረሻ ጊዜ ከባድ ተቃውሞ የተቀሰቀሰው በ2022 ሂጃብ በአግባቡ አልለበሰችም የተባለች ሴት ከተገደለች በኋላ ሲሆን በወቅቱ በተቃውሞው 550 ሰዎች ተገድለው ከ20ሺህ የሚልቁ ሰዎች ታስረው ነበር።
ከ100 በላይ ከተሞች በላይ የተስፋፋው የአሁኑ ተቃውሞ መልከ ብዙ ሲሆን ብዙዎቹ ሃገራት የኢራን መንግስት በተቃዋሚዎች ላይ የወሰደውን እርምጃ አውግዘዋል።
አሜሪካና እስራኤልን ጨምሮ የኢራን ተፃራሪ የሆኑ ሃገራትም በ1979 በአብዮት የመጣው የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ በዚህ ተቃውሞ ይፈርሳለ ብለው እየጠበቁ ይገኛሉ።
በተጨማሪም የኢራንን የአየር ክልል የሚያቋርጡ በረራዎች እየተሰረዙ ይገኛሉ።