ፋኖ በደብረብርሃን ከተማ በእቴጌ ጣይቱ እና በአፄ ዘርዓያዕቆብ ክፍለ ከተሞች ውጊያውን በበላይነት ተቆጣጥሮ ድል መቀዳጀቱን አስታወቀ!

ፋኖ በደብረብርሃን ከተማ በእቴጌ ጣይቱ እና በአፄ ዘርዓያዕቆብ ክፍለ ከተሞች ባደረገው ውጊያ አማራዊ ጀግንነትን ከጦር ሣይንስ እውቀት ጋር ያጣመረ ማጥቃት በመሰንዘር ውጊያውን በበላይነት ተቆጣጥሮ ድል መቀዳጀቱን አስታወቀ!

በአፋብኃ ደቡብ ዐምሓራ ቀጠና አሳምነው ዕዝ ዓፄ ዘርዓያዕቆብ ኮር ስር ከሚገኙት ከነጎድጓድ ክ/ጦር የተወጣጡ የፋኖ አሃዶች ትናንት ጥር 05/2018 ዓ/ም ማለዳ ጀምሮ እስከ ምሽት በደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ስር በሚገኙ ሁለት ክፍለ ከተሞች ውስጥ በነበሩ የአገዛዙ ወታደሮች ላይ ውጊያ በመክፈት ድል ተቀዳጅተው መዋላቸውን መረብ ሚዲያ ከዕዙ ሕዝብ ግንኘነት መምሪያ ለማረጋገጥ ችሏል።

ውጊያው የተከፈተው በከተማ አስተዳደሩ ስር በአፄ-ዘርዓያዕቆብ ክፍለ ከተማ ውስጥ በሚገኙ መጥቆሪያ ቀበሌ እና ወርቅጉር ገብርኤል በተባሉ አከባቢዎች እንዲሁም በእቴጌ ጣይቱ ክፍለ ከተማ ደግሞ ዘንዶጉር እና በዞ በተባሉ አከባቢዎች ላይ ነው።

አገዛዙ ሚኒሻና አድማ ብተና በተባሉ ባንዳዎች መንገድ መሪነት ከከባባድ መሣሪያ የታጠቁ ኤሊት ፎርስ ብሎ የሚጠራቸውን በርካታ የአየር ወለድ ኮማንዶዎችን በጎሽባዶ፡ አራዳ፡ መጥቆሪያ እንዲሁም በካሲማ በዞ አቅጣጫ መነሻቸውን ከኩየለሽ በማድረግና እንዲሁም በሌሎች የክፍለ ከተሞቹ አከባቢዎች ያሰለፈ ቢሆንም፡ ነገር ግን ወታደሮቹ ከወደ ፋኖ የተሰነዘረባቸውን ጥቃት መቋቋም ባለመቻላቸው እርስ በእርሳቸው ግጭት ውስጥ ገብተው መዋላቸውን መረብ ሚዲያ ለማረጋገጥ ችሏል።

በውጊያው “ባልሆነ አቅጣጫ መርታችሁ አስመትታችሁናል” በሚል ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ የአድማ ብተናና የሚኒሻ አባላት መረሸናቸው ታውቋል።

በተለይ ፋኖ በወሰደው የመከላከልና የመልሶ ማጥቃት እርምጃ ውጊያውን በበላይነት እየመራ በመዋሉ “ከድተው ወደ ፋኖ ሊቀላቀሉ ይችላሉ” በሚል ጥርጣሬ ብቻ በርካታ የአማራ ተወላጅ የሆኑ ኮማንዶዎች አስቀድሞ ተዘጋጅቶ በነበረ መች ኃይል ከበስተጀርባ ተወግተው መገደላቸውን የመረብ ሚዲያ ወታደራዊ ምንጮች መረጃውን አድርሰውናል።

በተጨማሪም ጓዶቻቸው የተረሸኑባቸው የሚኒሻና አድማ ብተና ኃይሎች “አገዛዙን እናገልግል ባልን እንዴት እንገደላለን” የሚል ጥያቄ ሲያቀርቡ “እናንተ ግልገል ፋኖ ናችሁ” የሚል ምላሽ የተሰጡ ሲሆን፡  በዚህ ምክኒያትም ከባድ ፍጥጫ ተፈጥሮ ማደሩ ነው የታወቀው።

አገዛዙ የአማራ ተወላጅ የሆኑ ወታደሮቹን ጨምሮ “ግልገል ፋኖ” ብሎ በሚጠራቸው በሚኒሻና በአድማ ብተና አባላት ላይ በውጊያ ወቅት ከበስተጀርባ ጥቃት ፈፅሞ ከመግደል ጀምሮ በቀጥታ እስከመረሸን የሚፈፅመውን ድርጊት አጠናክሮ በመቀጠል የውሻ ሞት እንዲሞቱ እያደረጋቸው እንደሚገኝ መረብ ሚዲያ አገዛዙን ከድተው የወጡ ወታደሮችን ዋቢ በማድረግ በተደጋጋሚ መዘገቡ አይዘነጋም።