እውቅ የፖለቲካ እስረኞች ጉዳያቸው ፖለቲካዊ መፍትሄ አግኝቶ ከእስር እንዲፈቱ ፍላጎት መኖሩ ተሰማ

(መሠረት ሚድያ)- ከሰሞኑ አንዳንድ የማህበራዊ ትስስር ገፆች አሁን ላይ በእስር ላይ የሚገኙ ፖለቲከኞችን፣ ጋዜጠኞችን እና ምሁራንን ጨምሮ ሌሎች የፖለቲካ እስረኞች በመንግስት ምህረት ተደርጎላቸው ሊፈቱ እንደሆነ የሚገልፁ መረጃዎች ሲያሰራጩ ነበር።

ይህን ተከትሎ መረጃውን የሚያጠናክር ወይም ሐሰትነቱን የሚገልፅ ማብራርያ ከመንግስት በኩል ባይሰጥም እነዚህ የፖለቲካ እስረኞች ጉዳያቸው ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲፈታ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ፍላጎት እንዳለው ሚድያችን የደረሰው መረጃ ይጠቁማል።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አቶ ብርሀኑ አዴሎ ታኅሣሥ 11 ቀን 2018 ዓ.ም. በፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ቂሊንጦ የጊዜ ቀጠሮ ማረፊያ ማእከል ተገኝተው ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት አቶ ዮሐንስ ቧያሌውን፣ አቶ ክርስቲያን ታደለን፣ ዶ/ር ወንደሰን አሰፋን፣ ዶ/ር ጫኔ ከበደን ፣ ዶ/ር ካሳ ተሻገርን፣ ዶ/ር ሲሳይ አውግቸውን እና ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይን አስጠርተው ማነጋገራቸው ታውቋል።

የሚድያችን ምንጮች እንዳረጋገጡት በዚህ ወቅት አቶ ብርሀኑ ከአማራ ክልል ግጭት ጋር በተገናኘ ተጠርጥረው በሕግ ጥላ ስር የሚገኙ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች፣ ማህበረሰብ አንቂዎች እና የሲቪል ማህበራት መሪዎች ጉዳያቸው የፖለቲካ መፍትሄ  እንዲያገኝ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ፍላጎት አለው ማለታቸው ታውቋል።

በ1997 ዓ.ም ከተካሄደው አገር አቀፍ  ምርጫ ጋር በተገናኘ ሁከትና ብጥብጥ ፈጥረዋል በሚል ተጠርጥረው የታሰሩ የቀድሞው ፖለቲከኞች ክሳቸው የተቋረጠው በፖለቲካ ውሳኔ መሆኑን ኮሚሽነሩ አስታውሰው አሁንም በሽብር ተጠርጥረው በእስር ላይ ያሉ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች እና ማህበረሰብ አንቂዎች ክሳቸው በፖለቲካዊ ውሳኔ እንዲቋረጥ ኮሚሽኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተነጋገረ ነው ብለው ምንጮች ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በጉብኝቱ ዙርያ በፌስቡክ ገፁ መረጃ ያጋራ ቢሆንም ሚድያችን በሰማው የፖለቲካ ውሳኔ አስፈላጊነት ዙርያ ያለው ግን የለም።

“በማእከሉ የተጠርጣሪዎች የሰብአዊ መብቶች አያያዝን አስመልክቶ በታዩ መልካም ለውጦች እና ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ላይ ከተጠርጣሪዎች ተወካዮች፣ ከማእከሉ እና ከፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን የሥራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት ተደርጓል” ያለው ኮሚሽኑ ተጠርጣሪዎች በማእከሉ ስለሚኖራቸው ቆይታ እና ስለሚያገኟቸው አገልግሎቶች በቂ ማብራሪያ የሚሰጣቸው መሆኑ አንዱ አበረታች ጉዳይ መሆኑን አንስቷል።

ይሁንና ማእከሉ መያዝ ከሚችለው የተጠርጣሪዎች ቁጥር በላይ የያዘ በመሆኑ ከፍተኛ መጨናነቅ መፈጠሩ፣ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ተጠርጣሪዎች ከሌሎች ተለይተው አለመያዛቸው፣ መዝጊያ የሌላቸው መጸዳጃ እና መታጠቢያ ቤቶችን ጨምሮ የተወሰኑ የውሃ ቧንቧዎች አገልግሎት ያቆሙ መሆናቸው መሻሻል የሚገባቸው ጉዳይ መሆናቸው በጉብኝቱ ወቅት ተነስቷል።

ሚድያችን የፖለቲካ እስረኞቹን ለመፍታት በመንግስት በኩል ፍላጎት እንዳለ ለማወቅ ጉዳዩ ይመለከታቸዋል ለተባሉት ለፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ በላይሁን ይርጋ ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርብም ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

-መሠረት ሚድያ-