ፖለቲከኛ ልደቱ አያሌው ከዩናይትድ ስቴትስ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይመለሱ የኢትዮያ አየር መንገድ የጉዞ ክልከላ አደረገብኝ አሉ። ፖለቲከኛው ዛሬ ባሰራጩት በፎቶ ግራፍ የተደገፈ የፅሁፍ መልዕክት ዛሬ የካቲት 3 ቀን 2017 ወደ ሀገር ቤት ለመመለስ አትላንታ አዉሮፕላን ማረፊያ ተገኝተው እንደነበር ገልጸዋል። ነገር ግን «የአገልግሎት ጊዜው ያላለፈ የኢትዮጵያ ፓስፖርት እና የተረጋገጠ የጉዞ ቲኬት ይዤ የተገኘሁ ቢሆንም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግን በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲን አነጋግሬ የተለየ ፈቃድ ካልተሰጠኝ በስተቀር ወደ ኢትዮጵያ መጓዝ እንደማልችል በአትላንታ የኢትዮዽያ አየር መንገድ ሀላፊ በሆኑት በአቶ ተሾመ ገ/ስላሴ ተነግሮኝ ተመልሻለሁ።» ብለዋል።
ፖለቲከኛው አክለው « በአሸባሪነት ወንጀል ሊከሰኝ እንደሚፈልግና በቁጥጥር ስር እንድውል ከኢንተር-ፖል ጋር ጭምር እየተነጋገረ እንደሆነ ሲገልፅ የነበረው የኢትዮዽያ መንግስት ዛሬ በራሴ ፈቃድ ወደ አገሬ ለመመለስ ስሞክር በእኔ ላይ ህገ-ወጥ ክልከላ ማድረጉ አስገርሞኛል።» ብለዋል። «መንግስት እኔን በወንጀለኛነት ከጠረጠረኝ ሊከሰኝና ሊያስረኝ ይችላል እንጅ ወደ አገሬ እንዳልገባ ሊከለክለኝ አይችልም።» ያሉት ልደቱ «የሀገሩን የጉዞ ሰነድ የያዘ ዜጋን ወደ ሀገሩ እንዳይገባ ለመከልከል የህግ ማዕቀፍ የለም» ብለዋል።

ክልከላውን ተከትሎ በሌላ አየር መንገድ ተጓጉዘው ወደ ሀገር ቤት እንደሚመለሱም አቶ ልደቱ አረጋግጠዋል።
አቶ ልደቱ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ጉዞ ስለመከልከላቸው አየር መንገዱ ለጊዜው ያለው ነገር የለም ።
አቶ ልደቱ በግንቦት 2015 በኢትዮጵያ መንግሥት ፤ መንግሥትን ለመገልበጥ በማሴርና በአሸባሪነት መጠርጠራቸውን ተከትሎ ከዩናይትድ ስቴትስ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመለሱ ተናግረው ነበር። በፈቃዳቸው ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው የቀረበባቸውን ውንጀላ በፍርድ ቤት ለመከራከር ዝግጁ መሆናቸውንም በተለይ ለዶቼ ቬለ በሰጡት ቃለምልልስ ገልጸው ነበር።
አቶ ልደቱ ለአምስት ወራት በእስር ላይ ከቆዩ በኋላ ለህክምና ወደ አሜሪካን ሀገር ተጉዘው ያለፉትን ሶስት ዓመታት ከ10 ወር ገደማ በዚያ ቆይተዋል።