‹‹ሕወሓት ሲፈልግ መንግሥት ሲፈልግ ፓርቲ ወይም ሕዝብ ነኝ ማለቱን ትቶ እንደ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ መንቀሳቀስ አለበት›› ጌታቸው አሰፋ (ፕሮፌሰር)፣ ፖለቲካ ተንታኝ

ምርጫ ቦርድ ለሕወሓት የሰጠውና እስከ የካቲት 3 ቀን 2017 ዓ.ም. ድረስ ባሉት ቀናት ጠቅላላ ጉባዔ እንዲያደርግ የሚያስገድደው ማሳሰቢያ ቀነ ገደቡ ነገ ያበቃል፡፡ የካቲት 11 የሕወሓት 50 ዓመት የወርቅ እዮቤልዩ በዓሉን ለማክበር በሁለቱም የሕወሓት ቡድኖች ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡ በእነ ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (/) የሚመራው ሕወሓትም ሆነ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ሕወሓት የየራሳቸውን የበዓል አከባበር ኮሚቴ መሥርተው ዝግጅት ጀምረዋል፡፡ በትግራይ ክልል ያለው የሁለቱ የሕወሓት ቡድኖች የእርስ በርስ ውዝግብ ገና አልተቋጨም፡፡ ገለልተኛ የነበረውን ጦሩንም በጉዳዩ ጣልቃ እንዲገባ አድርጎታል፡፡ ሕዝቡ በዚህ መሀል ተከፋፍሏል፡፡ የፌዴራል መንግሥቱ ከረጅም ጊዜ ዝምታ በኋላ ከሰሞኑ በትግራይ ጉዳይ አቋሙን አንፀባርቋል፡፡ለትግራይ ሕዝብ ምክርበሚል ርዕስ ይፋ በተደረገው የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (/) መልዕክት፣ የትግራይ ሕዝብ ካሳለፈው ሰቆቃ ተምሮ የጦርነት ቅስቀሳ የሚያደርጉ ኃይሎችን በቃ እንዲላቸው ጥሪ ቀርቧል፡፡

ይህን የጠቅላይ ሚኒስትሩን መግለጫ ተከትሎ ትግራይ ክልል ወዴት ያመራል የሚለው ብዙዎች በትኩረት የሚከታተሉት አሳሳቢ የፖለቲካ ጉዳይ ሆኗል፡፡ በዚህና በሌሎችም የትግራይ ክልልን አጠቃላይ ሁኔታ በተመለከቱ ነጥቦች ላይ፣ በትግራይ ፖለቲካ ትንተና በመስጠት ከሚታወቁት ምሁር ከጌታቸው አሰፋ (ፕሮፌሰር) ጋር ሪፖርተር ቆይታ አድርጓል፡፡ ከስድስት ዓመታት በፊት በኢሕአዴግ የሥልጣን ማብቂያ ዋዜማ ወቅት “የኢሕአዴግ ዕጣ ፈንታ በድርጅታዊ ፊዚክስ ዓይን” በሚል ርዕስ ትኩረት ሳቢ ትንተና በሪፖርተር ጋዜጣ ያስነበቡት ጌታቸው (ፕሮፌሰር) እንኳን ፓርቲ፣ ‹‹መንግሥትና አገር ቀርቶ ቤተሰብም ቢሆን በጋራ ተሳስሮ እንዲቀጥል የሚያደርግ አዲስ ኃይልና ጉልበት በየጊዜው መፍጠር ካልቻልክ ይፈርሳል›› በማለት ይህ በፊዚክስ የተረጋገጠ የተፈጥሮ ሕግ በሕወሓትም ሆነ በሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች ላይ የሚሠራ መሆኑን በመጥቀስ ለኢሕአዴግ የጻፉትን ትንተና ሰዎች ስሙን በሕወሓት ቀይረው እንዲያነቡት ነው የሚጋብዙት፡፡ የካናዳው ካግሊያሪ ዩኒቨርሲቲ መምህሩ ጌታቸው (ፐሮፌሰር) ከዮናስ አማረ ጋር ስለሕወሓትና ስለትግራይ ፖለቲካዊ ዕጣ ፈንታ ያደረጉት ሰፊ የቆይታ ጥንቅር ቀርቧል፡፡

ሪፖርተር፡- የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ (መልዕክት) እንዴት አዩት?

ጌታቸው (ፕሮፌሰር)፡- የዛሬ ሦስት ዓመታት በፊት በጦርነቱ ዋዜማ በነበርንበት ወቅት የነበረውን ስሜት ነው የፈጠረብኝ፡፡ ቃላት ሳይቀየር ሳይለወጥ ያን ጊዜ ይወጡ የነበሩ መግለጫዎችን የሚያስታውስ ሆኖ የወጣ መግለጫ ነው የሆነብኝ፡፡ እናቶች እንዳያለቅሱ፣ ቤቶች እንዳይፈርሱ፣ ሕዝቡ እንዳይጎዳ የሚሉ ቃላቶች አሉበት፡፡ ይህ ብቻም አይደለም መግለጫውን ተከትሎ በአዲስ አበባ የተደረገው ሠልፍም መልዕክቱ ከዚያን ጊዜው ሁኔታ ጋር ይመሳሰላል፡፡ በሚዲያዎች ነገርየው የተስተጋባበት መንገድም ቢሆን በቅድመ ጦርነት የነበረውን ሁኔታ ነው ያስታወሰኝ፡፡ ዳግም ጦርነት እየመጣ ነው የሚል ስሜት ነው የፈጠረብኝ፡፡ መንግሥት ወንጀለኛ የሕወሓትን መሪዎች አቀርባለሁ ቢል ችግር የለውም፡፡ ነገር ግን በዚህ ሰበብ የሲቪሎች ዕልቂት ድጋሚ የመከሰቱ ሥጋት አይቀሬ በሆነበት ይህን መሰል ማሳሰቢያ መስጠት አስፈሪ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ጦርነት አይቀሬ ነው የሚል ግምት አለዎት?

ጌታቸው (ፕሮፌሰር)፡- የቀደመውንም ጦርነት ቢሆን ማስቀረት ይቻል ነበር ብዬ ስለማምን፣ አሁንም ቢሆን የጦርነት ዝግጅት ካለ ከመከሰቱ በፊት ማስቆም ይቻላል ብዬ አምናለሁ፡፡ ለሥልጣን የሚዋጉ ተዋጊ ኃይሎች ሁሌም ቢሆን ታገስን፣ ገባን የሚል አመክንዮ ነው የሚሰጡህ፡፡ በእኛ አገር የተደረጉ ጦርነቶች ብዙዎቹ ግን መቅረት የሚችሉ ነበሩ፡፡ ከውጪ ሊወረን ከመጣ ኃይል ጋር ካደረግናቸው ጦርነቶች በስተቀር አብዛኛዎቹ መቀልበስ ይችሉ ነበር፡፡ ተገደን የገባንበት ነው የሚለው አያሳምነኝም፡፡ የሆነ ነገር እንዲለወጥ ሰው መሞትና ደም መፍሰስ የለበትም፡፡ የተራዘመም ቢሆን በድርድር ወይም በሚስጥር በሽምግልና ነገሮችን ጨርሰህ፣ ብዙ ዋጋ የሚከፈልበትን ቀውስ ማስቆም ትችላለህ፡፡ ጦርነት በሌለበት ወቅት የሚያድጉ ልጆች ዓይተህ ከሆነ ከአካላዊ ጀምሮ በሥነ ልቦና ጤናማ ትውልድ ነው የሚሆኑት፡፡ ጦርነት ባለበት አልሚ ምግብ ብቻ አይደለም የምታጣው፡፡ አልሚ ሐሳቦችንም አታገኝም፡፡ ጦርነት የትውልዱን ሥነ ልቦና ሁሉ የሚያቀነጭር ነው፡፡ አሁን ላይ ጦርነቱ አልተጀመረም፡፡ ስለዚህ ማስቀረት ይቻላል ብዬ እገምታለሁ፡፡ ዋና ዋናዎቹ ተዋንያን ጦርነቱን ማስቀረት ይፈልጋሉ ወይ የሚለው ነው ትልቁ ጥያቄ፡፡ የሕወሓት ጽሕፈት ቤት ቡድን ምርጫ ቦርድ የሰጠው ጉባዔ የማድረግ ቀነ ገደብ ደርሶበታል፡፡ ከዚህ በፊት ሕገወጥ ምርጫና ጉባዔ ነው ያደረከው ተብሏል፡፡ ሕወሓት ከአቋሙ ተመልሶ የተጠየቀውን ለማድረግ ዳገት እንደሚሆንበት ሁሉ፣ በአዲስ አበባ ያለው መንግሥትም እኔ ያልኩትን ካላደረክ ጦርነት ይጀመራል የሚል አቋም ላይ ለመድረስ አይቸገርም፡፡ ይህ ደግሞ ምናልባት ጦርነቱ እየመጣ ነውንዴ? የሚል ቅዠታዊ ሥጋት ፈጥሮብኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ሕወሓትን በተመለከተስንፈተ ፖለቲካ የገጠመው ቡድንየሚል አገላለጽ ይጠቀማሉ፣ ይህ ምን ማለት ነው?

ጌታቸው (ፕሮፌሰር)፡- የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደርን በተመለከተ ስንፈተ ሥልጣን የገጠመው ኃይል ነው የሚል ብይን ነው የምሰጠው፡፡ ይህን የምለው ደግሞ የመንግሥትን ሥልጣን ይዞ፣ ነገር ግን ብዙ ውስንነቶች ያሉበት በመሆኑ ነው፡፡ ምክር ቤት እንኳን የለውም፡፡ ሌላም ብዙ ችግሮችም ያሉበት ነው፡፡ በትግራይ ፖለቲካ በብቸኝነት ወሳኝ ድምፅ ይዞ ከቆየው ከሕወሓት ኃይል በተጨማሪ፣ የሌሎች የትግራይ ፖለቲካ ኃይሎችን ድምፅን በተወሰነ ደረጃ አሳትፎ የተመሠረተ ነው፡፡ የትግራይ ወጣት ለለውጥ የነበረው ድጋፍም ተጨማሪ ተነሳሽነት የሚፈጥር አጋጣሚ ሆኖለት ነበር፡፡ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ይህንና ሌሎችንም መልካም አጋጣሚዎች እንደመሠረት ተጠቅሞ ብዙ ነገር መሥራት የሚችል የነበረ ቢሆንም፣ ነገር ግን ምንም ሳይሠራ የቆየ ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ነው እንግዲህ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ስንፈተ ሥልጣን ገጥሞታል የምለው፡፡ እጁ ላይ ያለውን ሥልጣን ያልተጠቀመ በመሆኑ በዚያ መንገድ ነው መገለጽም የሚችለው፡፡ ሕወሓትን በተመለከተ ግን ሁሉንም ነገር አድራጊ ሆኖ የቆየ ድርጅት ነው፡፡ ሚዲያውን ፕሮፖጋንዳውን የተቆጣጠረ ኃይል ነበር፡፡ በተለይ ከኢሕአዴግ መፍረስ በፊት ባንኩም ታንኩም እንደሚባለው ከፍተኛ የሥልጣን ክምችት በእጁ ነበር፡፡ እኔ የማንም ፖለቲካ ፓርቲ አባል አይደለሁም፡፡ ነገር ግን ከውጪ ሆኜ እንደምታዘበው ሕወሓት የራሱ ኮምፎርት ዞን ነበረው፡፡ በራሱ ምኅዳር የፈለገውን ነገር እየሠራ የሚኖር ድርጅት ነበር፡፡ ነገር ግን አሁን ከዚያ ኮምፎርት ዞኑ ወይም ከራሱ ሜዳ ወጥቶ እንዲጫወት የተገደደበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በዚህ የተነሳም ብዙ መደናበር ሲፈጠርበት ይታያል፡፡ አሁንም በተቀየረ የጨዋታ ሜዳ ላይ ሆኖም ለመደገፍ ያሻውን ለማድረግ የመፈለግ ዝንባሌ ይታይበታል፡፡ ነባራዊው ሁኔታ ሕወሓት እንደፈለገው በፍጹም የበላይነት ያሻውን እያደረገ መቀጠል የሚፈቅድ አለመሆኑ ይታያል፡፡ በዚህ የተነሳ ብዙ ችግሮች በትግራይ ፖለቲካ ውስጥ እየተፈጠሩ ናቸው፡፡ በትግራይ አሁንም ብዙ ሰው ሕወሓትን እንደ አንድ የፖለቲካ ድርጅት ወይም ፓርቲ ማየት ገና አልለመደም፡፡ ከሥነ ልቦና ጀምሮ በተግባር ሲመነዘር ብዙ ችግር የሚመጣው በዚህ የተነሳ ነው፡፡ በእኔ ግምት ሰዎች የተለያዩ ፓርቲዎችን ሊደግፉ ይችላሉ፡፡ ሆኖም ግን አንድ የሆነ የጋራ መንግሥት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ጤነኛ ማኅበረሰብ አንድ የጋራ መንግሥት እንደሚያስፈልገው ሁሉንም ያግባባል፡፡ ነገር ግን ይህ በሥልጣን ላይ የሚቀመጠው መንግሥት የሚጠበቅበትን ከመሥራት ይልቅ ተቀምጦ ማዶ ማዶውን የሚጠብቅ ከሆነ ዋጋ የለውም፡፡ እንደ መንግሥት የሚሠራ፣ እንደመንግሥት የሚራመድ፣ እንደ መንግሥት የሚቆምና የሚቀመጥ መሆን ይኖርበታል፡፡ የአቶ ጌታቸው ጊዜያዊ አስተዳደር ይህን እያየሁበት ባለመሆኑ ነው ስንፈተ ሥልጣን ገጥሞታል የሚል ድምዳሜ የሰጠሁት፡፡

ሪፖርተር፡- ሕወሓትስ በምን ብያኔ ይገለጻል?

ጌታቸው (ፕሮፌሰር)፡- በነገራችን ላይ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ዋና ዋና ችግሮች ምንጭ፣ ገፊም ሆነ ሳቢ ሕወሓት ነው፡፡ ይሁን እንጂ የራስህን ድርሻና ኃላፊነት ተወጥተህ ነው ሌላው አደናቀፈኝና ጎተተኝ ማለት የምትችለው፡፡ ሕወሓት እኮ ከሕዝቡ ሥነ ልቦና ጀምሮ የማይቆጣጠረው ነገር አልነበረም፡፡ ሁሉን ነገር ሲቆጣጠር ነው የኖረው፡፡ ያንን ደግሞ አሁንም ማስቀጠልና በነበረው መሄድ ነው የሚፈልገው፡፡ የሚወስዳቸው ዕርምጃዎችም ሆነ ፍላጎቱና ሙከራዎቹ በሙሉ እሱን ነው የሚያሳዩት፡፡ ሕወሓት ግን አንድ ፓርቲ መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ መንግሥትም፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎችም፣ ቤተ እምነቶችም፣ ማኅበረሰቡ በሙሉ ሕወሓት እንደ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ መንቀሳቀስ አለበት ብሎ መገሰፅ አለበት፡፡ ልክ እንደተቃዋሚ ፓርቲዎች ሁሉ ሕወሓትም ከማንም ሳይበልጥና ሳያንስ በእኩል ሊታይ የሚገባው ፓርቲ ነው፡፡ እንደሌሎች ፓርቲዎች ሕግ አክብሮ ሊንቀሳቀስ ይገባል የሚለው ገዥ አተያይ እስካልተፈጠረ ድረስ፣ ሕወሓት በለመደው መንገድ ካልሄድኩ ብሎ ማስቸገሩ የሚቀጥል ነው የሚሆነው፡፡ ከሕዝቡ ጋር የተለየ ትስስር ያለኝ ፓርቲ ነኝ ማለቱ፣ የተለየ ቦታ ይገባኛል፣ ሲፈልግ ራሱን መንግሥት አድርጎ ማየቱ፣ሲፈልግ ደግሞ ራሱን እንደ ሕዝብ አድርጎ መመልከቱ የተለመደ ነው፡፡ ሆኖም ይህ በጣም አደገኛ ልምምድ ጭምር ነው፡፡ ሕወሓት ፖለቲካን ከመሠረተ ትምህርት ነው መጀመር ያለበት፡፡ ጠንካራ ነኝ ሕዝባዊ መሠረት ያለኝ ፓርቲ ነኝ ሊል ይችላል፡፡ ነገር ግን እሱ በሕዝብ ድምፅ ነው በምርጫ መወሰን ያለበት፡፡ ከዚያ ውጪ ግን ከሌሎች ፓርቲዎች እኩል ነው መሆን ያለበት፡፡ ከመንግሥት ምንም የተለየ ጥቅም ማግኘት የለበትም፡፡ ከአባላቱ በሚደረግ መዋጮ መኖር ይችላል፡፡ በመንግሥትና በፓርቲ መካከል መደበላለቅ ብዙ ይታያል፡፡ ይህ ደግሞ ሲደረግ የነበረው ሆን ተብሎ እንጂ ባለማወቅ አይመስልም፡፡ ሲፈልግ ፓርቲ ነው፣ ሲፈልግ ደግሞ መንግሥት ሆኖ ጥቅሞቹን በተሻለ መንገድ ያስከብራል፡፡ ሲያሻው ደግሞ ሕዝብ ነኝ ይላል፡፡ ይህ ማምታታት መቆም አለበት፡፡

ሪፖርተርትግራይ አሁን ያለበት የቀውስ ሁኔታ ይታወቃል፡፡ ኃላፊነት እናከፋፍል ብንል ለማን ምን ዓይነት ተጠያቂነት ነው የምንሰጠው?

ጌታቸው (ፕሮፌሰር)፡- ለእኔ የአዲስ አበባው፣ የባህር ዳሩና የአስመራው ኃይሎች ዋናዎቹ የጥፋት ምንጭ ናቸው፡፡ ከጦርነቱ ዕቅድ ጀምሮ እስከ ፍፃሜውና አሁንም እስካለው ችግር ድረስ ተጠያቂነት አለባቸው፡፡ ግን በኔ ዕይታ ተጠያቂነትን ለአንዱ ሰጥተህ ሌላውን ንፁህ የምታረግበት ሆኖ አይታየኝም፡፡ በዚያ ውስብስብ ችግሮች ባለበት የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ተጠያቂነት አይታወቅም፡፡ ጥፋት ትግራይ ውስጥም ሆነ ውጭም ይፈጸም፣ የምር በነፃ ፍርድ ቤት የሚገባውን ፍትሕ ስንሰጥ አይታይም፡፡ የትግራይን ቀውስ ተጠያቂነት ስናስቀምጥ፣ በሌላ በኩል በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች የትግራይ ኃይል (ሕወሓት) እኛ ላይ ግፍና ወንጀል ፈጽሞብናል የሚልም መኖሩ መታወቅ አለበት፡፡ የዛሬ ሦስት ዓመት ትዊተር (ኤክስ) ላይ እንዳጋራሁት፣ እኛ የአዲስ አበባው፣ የባህር ዳሩና የአስመራው ኃይል ተጋግዘው ዘር ማጥፋት ፈጽመውብናል እንላለን፡፡ ሌሎች ደግሞ የትግራይ ኃይል ግፍ ፈጽሞብናል ይላሉ፡፡ ስለዚህ ሁላችንም ተጋግዘን ሁሉንም አጥፊዎች ለምን ወደ ፍርድ አናመጣም›› ብዬ ጥያቄ አቅርቤ ነበር፡፡ እኔ አሁንም በዛ ነው የማምነው፡፡ በትግራይ ቢሆን ለምሳሌ ጦርነቱን ማስቀረት ይቻል ነበር ወይ? በምን መንገድ ውሳኔዎችስ ሲወሰኑ ነበር? የሚለው በአጣሪ ኮሚሽን መጠየቅ አለበት፡፡ የሕወሓት መሪዎች ፖለቲካውን ይመሩ ስለነበር፣ የትግራይ ጦር (ቲዲኤፍ) ኃይሎችም በጦርነቱ ስለነበሩ መደበላለቅ ሳይኖር እያንዳንዱ አካል እንደየተሳትፎው መጠየቅ አለበት፡፡ አንዳንድ ሰው ሕወሓት ነው ያጠፋው፣ ሕወሓት ነው ለሁሉም

ነገር ምንጭ ይላል፡፡ ሆኖም ብዙ ቁጥር ያለው የተባበረ ኃይል አሰማርቶ ግፍና በደል የፈጸመ ወገን በተቃራኒው አለ፡፡ ከዚያ ወዲህ ባለው ሁኔታ ደግሞ የውጭው ኃይል ጣልቃ ገብነት እንዳለ ቢሆንም፣ የሕወሓትና የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፍትጊያም ቢሆን ተጠያቂነት የሚያመጣ ነው፡፡ ሕወሓትና ጊዜያዊ አስተዳደሩ የሚያደርጉት መሳሳብ ግፍ የደረሰበት ሕዝብ የሚመሩ አይመስሉም፡፡ ይህም ቢሆን ወንጀል ነው፡፡ ለዚህ ወንጀለኛ ማነው ብትለኝ ደግሞ ሕወሓትና ጊዜያዊ አስተዳደሩ ናቸው ነው የምልህ፡፡ አራት ኪሎ ያለው መንግሥት ነገሩን በማጋጋልና የተለያዩ ነገሮች በማድረግ የሚፈጥረው ችግር እንዳለ ሆኖ ተጠያቂነት ከነዚህ አይወጣም፡፡

ሪፖርተርትግራይ ክልል ወዴት እየሄደ ነው? ከቀውስ ወደቀውስ ወይስ?

ጌታቸው (ፕሮፌሰር)፡- ይህ በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ ትግራይ ምን መሆን አለባት ብዬ የማምነውን ልናገር፡፡ ሕዝቡን በነፃነት እንዲያስብ፣ በነፃነት እንዲንቀሳቀስ፣ በሰላም እንዲኖርና  በሰላም እንዲንቀሳቀስ ማድረግ ነው፡፡ ሌላው መሠረታዊ ነገር ደግሞ ፍትሕ ማግኘት ነው፡፡ ላለፉት 20/30 ዓመታት ለተፈጸሙም ሆነ አሁንም እየተፈጸሙ ላሉ ወይም ወደፊትም ለሚፈጸሙ ወንጀሎች፣ በፍትሕ አደባባይ የሚዳኝበት ሥርዓት ሕዝቡ እንዲፈጠርለት ነው የምፈልገው፡፡ የሕወሓት ኃይሎች በጣም እየተሳሳቡ ነው፣ በዚህ ላይ ከፍተኛ የጦርነት ሥጋትም አለ፡፡ ነገር ግን ትግራይን ሳስብ ተስፋ ነው የሚታየኝ፡፡ የትግራይ ሕዝብ ያሉበት ችግሮች እንዳሉ ሆነውም ወደጥሩ መንገድ እየሄደ እንደሆነ ነው የሚሰማኝ፡፡ ከዚያ አንድ ፓርቲ ፍፁም የበላይ ሆኖ አንድም ሦስትም ሆኖ እየተጫወተ የሚኖርበት አካሄድ እየተቀየረ ነው፡፡ ሕወሓት መንግሥትም፣ ፓርቲም፣ ሕዝብም ሆኖ የሚጫወትበት ሜዳ እየተለወጠ ነው፡፡ የወጣቱን ሥነ ልቦናም ሆነ የሕዝቡን ፍላጎት ብታይ ይህ እንዲቀየር በትግራይ መንገድ መጀመሩን በደንብ ትረዳለህ፡፡ ለጊዜውም ቢሆን እያየሁት ያለሁትና ወደፊትም እያደገ ይስፋፋል ብዬ ተስፋ የማደርገው፣ የሁለቱን ሕወሓቶች ውዝግብ ሚዲያው እያስተናገደበት ያለበት ሁኔታ ነው፡፡ በኢፈርት ሥር ያለው የድምፀ ወያኔ ሚዲያ ሳይቀር ሁኔታውን የሚሸፍንበት መንገድ ነፃነትና ዴሞክራሲያዊነት የሚታይበት ነው፡፡ እስካሁን ወደ ጦርነትና ወደ ጠብመንጃ መማዘዝ አልገቡም፣ እስካሁን የሚያደርጉት የቃላትና የሐሳብ ፍጭት በሚዲያ በእኩል እየተስተናገደ ነው፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ የነበረው የሠራዊቱ አቋም በዚህ መካከል አልገባም የሚል ነበር፡፡ ነገር ግን ከሰሞኑ ለአንዱ ያዘነበለ መግለጫ በመስጠት ማኖ ነክቶ ነበር፡፡ ያም ቢሆን ከሕዝቡ የመጣው ቁጣና በሰላማዊ ሠልፍ ጣልቃ አትግቡ ብሎ መገሰጹ ተስፋ የሚያሳድር ነው፡፡ ከወጣቱ ከሌላውም የኅብረተሰብ ክፍል የመጣው ግብረ መልስ፣ ጦር ኃይሉ ሰብሰብ እንዲል አድርጎታል፡፡ ይህ ሁሉ በሰላም ይቀጥላል ብዬ በማሰብ ትግራይ ወደጥሩ ነገር እየሄደች ነው የሚል ተስፋን አሳድራለሁ፡፡ ይህም ሆኖ ግን በትግራይ አሁንም ያልተፈታ ገና ብዙ ጥያቄ መኖሩን መጥቀስ አለብኝ፡፡ የትግራይ ግዛታዊ አንድነት ጉዳይ አለ፣ የተፈናቃዮች ጉዳይ አለ፡፡ በአንዳንድ የተፈናቃይ ጣቢያዎች ሕፃናት በረሃብና በመድኃኒት ዕጦት ሲሞቱ ማየት በዚህ ዘመን ሊፈቀድ የማይገባው ጥፋት ነው፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ ግን ወደተሻለ መንገድ እየሄደ ነው የሚመስለኝ፡፡ ይህን እያወራን ባለበት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አማካሪ ምክር ቤት ማቋቋሙን ይፋ አድርጓል፡፡ ቅድም እንዳልኩት ስንፈተ ሥልጣን ካልያዘው በስተቀር ይህም ጥሩ ዕርምጃ ነው፡፡ በአጠቃላይ ግን ትግራይ በቀውስ ውስጥ ሆኖም ጥሩ ተስፋ ይታየኛል፡፡

ሪፖርተርሕወሓት የሌለበትና ከፖለቲካ ገለል ያለበት ሁኔታ በትግራይ ይመጣል ብለው ያስባሉ?

ጌታቸው (ፕሮፌሰር)፡- ገለል ማለት ምን ማለት ነው የሚለውን እንጠይቅ፡፡ ሕወሓት ከሌለ ትግራይ የለም፣ ሕወሓት እንዲህ ከሆነ ምናምን የሚሉ አስተያየቶች ብዙ ጊዜ ይሰማሉ፡፡ ይህን በጣም ጨዋ ሆነህ ግለጸው ከተባልኩ ድንቁርና ነው የምልህ፡፡ ሕወሓት ራሱ ዕድሜውን ከቆጠርከው አሁን በቅርቡ 50 ዓመት ይሞላዋል፡፡ ትግራይና የትግራይ ሕዝብን ደግሞ ለስንት ሺሕ ዓመታት እንደኖሩ የምታውቀው ነው፡፡ ሕወሓት ገለል ይደረግ ሲባል በሁለት መነጽር የሚታይ ነው የሚሆነው፡፡ አንዱ በሕግ መነጽር ሲሆን፣ ሕወሓት ወንጀል የፈጸመ ድርጅት ነው ብሎ የሚከስ በመሰለኝና ደሳለኝ ሳይሆን በሕግ አደባባይ ከሶ መርታትና ወንጀለኝነቱን ማረጋገጥ መቻል ነው ያለበት፡፡ ሌላው ግን ሕወሓት ገለል የሚለው በአባላቱና በሕዝቡ ውሳኔ ነው፡፡ አባላቱ በምርጫቸው አንፈልግም እንልቀቅ ወይም እንቀይረው ብለው ሊወስኑ ይችላሉ፡፡ ሌላው ደግሞ በይስሙላ ምርጫ ሳይሆን በሀቀኛ የምርጫ ሥርዓት ሕወሓትን አልፈልግህም ብሎ ሊወስን ይችላል፡፡ እንደ አንድ ፓርቲ ማለትም እንደ ሳልሳዊ ወያኔ ትግራይ፣ እንደ ውድብ ነፃነት ትግራይና እንደሌሎቹ ሁሉ በነፃነት ተወዳድሮ የተለየ ጥቅም ሳያገኝ መመረጥ ሲችል ነው ሊቀጥልም ላይቀጥልም የሚችለው፡፡ ‹‹ፓርቲ ፓርቲ ነው፣ መንግሥት መንግሥት ነው›› ብሎ ጊዜያዊ አስተዳደሩ በሕግ መደንገግም ማስፈጸምም አለበት፡፡ እኔ በምሠራበት ሚዲያ ጄኔራል ፃድቃንን፣ ጄኔራል ታደሰንም ሆነ አቶ ጌታቸውን አቅርቤ አወያይቻቸዋለሁ፡፡ ባለፉት ወራትና ዓመታት እኔ በግሌ የታዘብኩት ሕወሓትን እንደ ልዕለ ፓርቲ የመመልከት ዝንባሌ መኖሩን ነው፡፡ ሕወሓት ፓርቲ ብትሆንም ከሁሉም ፓርቲዎች በላይ ሆና ነው የምትታየው፡፡ ስትፈልግ ደግሞ መንግሥትም ሕዝብም ትሆናለች፡፡ ይህ ሁሉ ጥያቄ ሲመለስ ነው መገለል የሚለው ጥያቄ የሚመለሰው ማለት ነው፡፡

ሪፖርተርኤርትራ በቅድመ ጦርነት፣ በጦርነቱና በድኅረ ጦርነት ያላት ሚና ምንድነው?

ጌታቸው (ፕሮፌሰር)፡- በጣም ወሳኝና ሰፊ ጥያቄ ነው፡፡ የአስመራው ኃይል ከኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ የነበራትን ዓለም አቀፍ ተፅዕኖ ተጠቅማ ባደረገችው ጥረት፣ በኤርትራ መንግሥት ላይ ማዕቀብና ዓለም አቀፍ ጫና ሲደርስ ነው የቆየው፡፡ በሻእቢያ መንግሥት መሪ በኩል ይህ ከፍተኛ የበቀል ስሜት ያስቋጠረ ነበር፡፡ የፈለገውን ያክል ይፍጅ፣ የፈለገውን ያክል ኤርትራ ዋጋ ትክፈል እንጂ ያን ነገር ሊበቀሉ ቆርጠው ቀን ሲጠብቁ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ያ ማዕቀብና መገለል በኤርትራ ላይ ቢደርስም በሕዝቡ መካከል ግንኙነቱ እንዳይበጠስ ጥረት አድርጋለች፡፡ ለምሳሌ ብዙ ተማሪዎች ትግራይ ውስጥ በዩኒቨርሲቲዎች ደረጃ ጭምር ሲማሩ ነበር፡፡ በትግራይ ብዙ የስደተኞች መጠለያ ተከፍተው ኤርትራዊያን ሲጠለሉም ነበር፡፡ በዚያ ወቅት መንግሥት የሠራው ትልቅ ስህተት የምለው ነገሩን ሰላምም ጦርነትም ሳይፈጠር በነበረበት ተከድኖ ይብሰል ብሎ መተውን ነው፡፡ አሌክስ ደዋል እ.ኤ.አ. በ2015 በጻፈው መጽሐፍ ይህ ሁኔታ ያልተወራረደ የፖለቲካ ሒሳብ እንዲፈጠር ማድረጉን ገልጾት ነበር፡፡ ኤርትራ ከመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች በምታገኘው ገንዘብና መሣሪያ በሱዳንና በሶማሊያ በምታደርጋቸው ጣልቃ ገብነቶች ብዙ ችግር በኢትዮጵያ ላይ እንዲፈጠር ስታደርግ ቆይታለች፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ሲመጡ ደግሞ ሕወሓት የነበረውን መዋቅርና ጥንካሬ አይተው ለአራት ኪሎ ሥጋት እንደሆነ ማሰብ ጀመሩ፡፡ ይህ ደግሞ የአስመራው የሻእቢያ መንግሥት ለሕወሓት ከነበረው አመለካከት ጋር የሚዛመድ ሆነ፡፡ ጦርነቱ ጥቅምት ሊጀምር ከአንድ ወር በፊት የሻዕቢያ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ ምን ማድረግ እንደሚፈልግ የጻፈው ሰነድ ነበር፡፡ የሻዕቢያ የስዊድን ወኪል ነበር ሰነዱን ያወጣው፡፡ በትግራይ ላይ የዘር ማጥፋት ግንባር ሲፈጠር የፖለቲካም ሆነ የፕሮፖጋንዳ ሽፋን በመስጠት ወሳኝ ሚና የሻዕቢያ ኃይል ተጫውቷል፡፡ እንደሚታወቀው ደግሞ በጦርነቱ ከፍተኛ ጭፍጨፋ የተፈጸመባቸው አካባቢዎች ከአክሱም እስከ ማሪያም ደንገላት ድረስ የሻዕቢያ ኃይል የገባባቸው አካባቢዎች ናቸው ዋናዎቹ፡፡ ከዚያ በኋላ በብዙ ጥረት የፕሪቶሪያ ስምምነት ሲመጣም በትግርኛ ‹‹ተኮሊፍና ወይም ተደናቀፍን›› የሚል ንግግር ነው ኢሳያስ የተናገረው፡፡ ከዚያ ወዲህ የአስመራና የአዲስ አበባ መንግሥት በመካከላቸው አለመተማመን፣ መኮራረፍና አሁን እስከምናየው የውጥረት ዓይነት ስሜት ሲፈጠር ነው የታየው፡፡ በነገራችን ላይ በትግራይ በኩል ጦርነቱን ማስቀረት ይቻል ነበር ብለው ከሚያምኑ ጥቂት ሰዎች እኔ አንዱ ነኝ፡፡ የባህር ዳሩ፣ የአዲስ አበባውም ሆነ የአስመራው ኃይል

ወደ ጦርነቱ ግንባር ፈጥነው የገቡት የተለያዩ ፍላጎቶችን ይዘው ነው፡፡ የአዲስ አበባው መንግሥት የአራት ኪሎ ሥልጣን ብቻ ነው የሚገደው፡፡ የአስመራው መንግሥት በቀል ነው የሚፈልገው፡፡ የባህር ዳሩ ቡድን ደግሞ ግዛት ማስመለስ ነበር ፍላጎቱ፡፡ ስለዚህ ሕወሓት መቀሌ ላይ ተቀምጦ ከሚፎክር የአዲስ አበባውን መንግሥት ለሺሕ ዓመት ንገሥ ብሎ ዕውቅና ቢሰጥና ሥልጣኑን ባይገዳደር ጦርነቱን ማራቅ ይችል ነበር፡፡ አፋር ለምሳሌ በሁለት አገሮች መካከል የሚገናኝ ሕዝብ ነው፡፡ ሶማሌም በሁለት አገሮች መካከል የሚገናኝ ሕዝብ ነው፡፡ ኑዌርና ኑዌርም እንደዛው፡፡ ትግርኛ ተናጋሪ ሕዝብም በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል የሚገኝ ቢሆንም ነገር ግን ለረጅም ጊዜ እንዳይገናኝ ሲደረግ ነው የኖረው፡፡ ሻዕቢያ በራሱ ርዕዮተ ዓለማዊ ምክንያት ሁለቱን ሕዝብ ማቆራረጥ ዋና ስትራቴጂው አድርጎ ተጠቅሞታል፡፡ ወደ ጦርነቱ ሊገባ ሲል በጻፈው ሰነድ ላይ እንዲያውም በሁለቱ የትግርኛ ተናጋሪ ሕዝቦች መካከል ትግርኛ የማይናገር ማኅበረሰብን በማስፈር ጭምር ሁለቱን ማቆራረጥ ያስፈልጋል ብሎ ከትቦታል፡፡ ይህ እየመሠረቱት ላሉት በራሳቸው ፍላጎት ብቻ የተቀረፀች ኤርትራን የመፍጠር ግብ እንደ ስትራቴጂ ሊጠቀሙበት ሞክረዋል፡፡ በኤርትራ ትግርኛ የሚናገረው ማኅበረሰብ በኢትዮጵያ ካለው ትግርኛ ተናጋሪ ጋር ፍፁም በጠላትነት እንዲተያይና ተቆራርጦ እንዲቀር ነበር የሚፈልጉት፡፡

ሪፖርተርከኤርትራ ጋር አሁን ሕወሓት ጥምረት ለመፍጠር ይችላል?

ጌታቸው (ፕሮፌሰር)፡- ከአስመራው ኃይል ጋር አንድነት ለመፍጠር አይሞክሩም ብዬ አላስብም፡፡ ነገር ግን ተጠያቂነትን በተመለከተ እኔ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብዬ አስባለሁ፡፡ ከዛ ሁሉ ዕልቂት በኋላ ማንም ይሁን ማንም ከአስመራ ኃይል ጋር የሚያብር የትግራይ ፖለቲካ ኃይል መጠየቅ አለበት፡፡ ይህን የሚያደርግ ኃይል በቃ ለሆነው ሁሉ ነገር ምንም ግድ አይሰጠኝም የሚልና ራሱን ብቻ የሚያዳምጥ ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ይህን የሚያደርግ ወገን፣ በትግራይ ፖለቲካ ውስጥ ምንም ዓይነት ፖለቲካዊም ማኅበራዊም ቦታ ሊኖረው ይገባል ብዬ አላስብም፡፡ የሻዕቢያ ኃይል ግን መገለባበጡን ይችልበታል፡፡ አንዴ ከቃጣር፣ ሌላ ጊዜ ከሳዑዲ፣ አንዴ ከኢራን፣ ከዓረብ ኤምሬቶች እየተሻረከ የመጣ ኃይል ነው፡፡ ያኔ አማራን በሚመለከት ሲያራምድ የቆየውን ፖለቲካ ትቶ ከአማራ ኃይሎች ጋር ተጣምሮ ዛሬ ይታያል፡፡ አሁን ደግሞ ትግራይ ውስጥ ካሉ የሕወሓት አንጃዎች ጋር ግንባር ፈጥሮ ለመንቀሳቀስ ሲሞክር ይታያል፡፡ ሻዕቢያ የፈለገውን ቢሞክር፣ ነገር ግን ትግራይ ውስጥ ያን ሁሉ ወንጀሉንና ግፉን ረስቶ ግንባር ለመፍጠር የሚተባበር ኃይል ሊኖር አይገባም፡፡ በግሌ ምንም ዓይነት ጦርነት መፈጠር የለበትም ከሚሉት ወገኖች ውስጥ ነኝ፡፡ ነገር ግን ጦርነት አይቀሬ ከሆነ እንኳ ከሻዕቢያ ጋር ከመተባበር ከኢትዮጵያ ጋር ቆሞ የአስመራውን ኃይል ማስታገስ አስፈላጊ ነው ብዬ ነው የምናገረው፡፡

ሪፖርተርለትግራይ ምንድነው የሚበጀው፡፡ የፕሪቶሪያ ስምምነት ሙሉ ለሙሉ መተግበር፣ ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን ሥር ሆኖ መቀጠል፣ መገንጠል ወይስ ሌላ መንገድ?

ጌታቸው (ፕሮፌሰር)፡- የዛሬ ዓመትና ሁለት ዓመት ብትጠይቀኝ ለዚህ ግልጽ መልስ ነበረኝ፡፡ መንግሥት የሚባለው አካል አምባገነንም ይሁን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሱን ዜጎች ከምንም በላይ መጠበቅ ነው ኃላፊነቱ፡፡ ሆኖም ኃላፊነቱን ትቶ ራሱ ከውጪ ኃይል ጋር ከዘመተብህ በኋላ ይህ ጥያቄ ውስጥ ይወድቃል፡፡ ይህን ያደረገው ደግሞ በመላ በልሂቃኑ ጭምር ተደግፎ መሆኑ ሲታሰብ ነገሩ ከባድ ጥፋት ይሆናል፡፡ ትግራይ ራሱን መከላከል የሚችልበትና በራሱ መቆም ያለበት ሁኔታ መፈጠር አለበት ብዬ እከራከር ነበር፡፡ አሁን ላይ ሆኜ ከዚያ ወዲህ የተፈጠረውን የሁለቱን የሕወሓት አንጃዎች ፍትጊያ ካየሁ በኋላ ግን፣ ትግራይ ተገንጥላ አገርም ብትሆን፣ ልክ እንደ የሻዕቢያዋ ኤርትራ ትሆናለች የሚል ስሜት ነው ውስጤ የተፈጠረው፡፡ ገለልተኛ ሊሆን ይገባል የሚባለው ወታደሩ ጣልቃ ገብቶ ዲክታተራዊ ባህሪ ላንጸባርቅ ማለቱ፣ ክልሉ ቢገነጠልም እነዚህ ኃይሎች እንደ ሻዕቢያ ከመሆን የሚመልሳቸው የለም ብዬ እንድገምት አድርጎኛል፡፡ በክልሉ አሁንም የወጣቱ የዴሞክራሲ ፍላጎት ተስፋ ሰጪ ነው፡፡ ይህ ሳይቀለበስ መሄድና የትግራይ ሕዝብን በነፃነትና በሰላም የሚያኖር ከባቢ አየር መፍጠር አለበት ነው የምለው፡፡ ተገንጥለህ አገር ሆንክ ከሌሎች ጋር በፌዴሬሽን ተሰባስበህ ኖርክ፣ ዋናው ነገር በምትኖርበት አካባቢ ሰላም ትሆናለህ ወይም? ፍትሕና ዴሞክራሲ አለህ ወይ? የሚለው ጉዳይ ነው ወሳኙ ጥያቄ፡፡ በፊት ሌላ ቋንቋ ተናጋሪ ይጨቁነኝ ነበር፡፡ አሁን ግን የራሴን ቋንቋ የሚናገር ቢጨቁነኝ ይሻላል የሚል ከሆነ፣ ምርጫህ አገር የመሆኑ ፋይዳ ትርጉም የለውም፡፡ ለራሱ ክብር ያለው ማኅበረሰብ በራሴ ቋንቋ ተናጋሪዎች ልደፍጠጥ ወይም ልጨቆን አይልም፡፡ አሁንም ቢሆን ለትግራይ ይበጃል የምለው ግዛታዊ አንድነቱ ተመልሶ፣ የተፈናቀሉ ወደቀያቸው ተመልሰው፣ ተጠያቂነት ሰፍኖ፣ የዴሞክራሲና የፍትሕ መንገድን መከተል ነው፡፡ ይህ ከሆነ በኋላ አገር የመሆን ጥያቄ በሕዝቡ ነፃ ፍላጎትና ፈቃደኝነት መወሰን ይችላል ብዬ ነው የማስበው፡፡ የወጣቱ አብዛኛው ስሜትና ፓርቲዎች ጭምር ትግራይ አገር መሆን አለባት የሚል ፍላጎት ሲንፀባረቅ አያለሁ፡፡ አገር የመሆን ጥያቄ ግን አገር ለመባል ብቻ መነሳት የለበትም፡፡ አገር ተሆኖም እንደ ኤርትራ ፍፁማዊ አምባገነናዊ ሥርዓት እጅ ላይ የመውደቅ ዕድል አለኮ፡፡ ኤርትራውያን እንኳን ኤርትራ ውስጥ ውጭ አገር እየኖሩም ስለሻዕቢያ ትንፍሽ ማለትን ሲፈሩ ነው ያየነው፡፡ አገር በመሆን የሚገኘው እንዲህ ዓይነት አፈና ከሆነ ቢቀር ነው የሚሻለው፡፡ https://www.ethiopianreporter.com/138142/