የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር፣ በክልሉ የሚካሄዱ ወርቅና መዳብን ጨምሮ ማናቸውም የማዕድን ቁፋሮ ሥራዎች ከየካቲት 1 ጀምሮ ሙሉ በሙሉ እንዲቆሙ ውሳኔ ማሳለፉን የክልሉ ቴሌቪዥን ዘግቧል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ ይህን መመሪያ ያስተላለፈው፣ የክልሉ የማዕድን ሃብት በሕገወጥ መረቦች አማካኝነት እየተመዘበረ መኾኑን በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል። ጊዜያዊ አስተዳደሩ፣ በክልሉ የሚካሄደዱ መጠነ ሰፊ ሕገወጥ የማዕድን ቁፋሮዎችን የሚመረምር ግብረ ኃይል ማቋቋሙንም ቀደም ሲል ገልጦ ነበር።
በሕገወጥ የማዕድን ቁፋሮው የታጠቁ ቡድኖች በዋናነት እንደሚሳተፉና በተለይ የወርቅ የኮንትሮባንድ ንግድ መረብ እስከ አዲስ አበባ፣ አሥመራ፣ ካምፓላና ዱባይ ድረስ የተዘረጋ ስለመኾኑ በተደጋጋሚ እንደተዘገበ አይዘነጋም።