እናት ፓርቲ፣ መኢአድና ኢሕአፓ፣ ገዥው ብልጽግና ፓርቲ በቅርቡ ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ ራሱን “የስኬት ማማ” ላይ እንዳለ አድርጎ በመንግሥታዊ መገናኛ ብዙኀን አስነግሯል በማለት ዛሬ በጋራ ባወጡት መግለጫ ተችተዋል።
ገዥው ፓርቲ “አገራዊ ምስቅልቅሎሽ” ያመጣና “የሕዝብን አደራና ተስፋ ያስጨነገፈ” ፓርቲ ነው በማለት የወቀሱት ፓርቲዎቹ፣ ፓርቲው ራሱን በጥልቀት ገምግሞ በጋራ አገርን ለማዳን እንዲሠራ ምክረ ሃሳብ ለግሰዋል።
ፓርቲው ጦር መሣሪያ ካነሱ ከኹሉም ሃይሎች ጋር በአፋጣኝ ሠላማዊ ድርድር እንዲጀመርም ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው ጠይቀዋል።
ፓርቲዎቹ፣ ገዥው ፓርቲ የሚመራው መንግሥት በአገሪቱ በሰላምና ጸጥታ፣ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና ማኅበራዊ መስኮች ላይ ፈጥሮታል ያሉትን ምስቅልቅል በመግለጫቸው ዘርዝረዋል።