የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት በኢትዮጵያ እየጠበበ ነዉ  

በኢትዮጵያ በየጊዜው እየጠበበ መጥቷል ያለው የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት እንዳሳሰበው ሲ-ፒ-ጄ የተባለው የዓለም አቀፍ የጋዜጠኞች መብት ተቆርቋሪ ድርጅት አስታወቀ። ድርጅቱ በቅርቡ አደረኩት ባለው የዳሰሳ ጥናት እ.አ.አ ከ2020 ዓም ወዲህ ብቻ 54 ጋዜጠኞች በሙያቸው የተነሳ በደረሰባቸው ጫና አገር ጥለው እንደተሰደዱ ማረጋገጡን ጠቅሷል፡፡

አሳሳቢዉ የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ በየጊዜው እየጠበበ መጥቷል ያለው የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት እንዳሳሰበው ሲ-ፒ-ጄ የተባለው የዓለም አቀፍ የጋዜጠኞች መብት ተቆርቋሪ ድርጅት አስታወቀ ፡፡ ድርጅቱ በቅርቡ አደረኩት ባለው የዳሰሳ ጥናት እንደአውሮፓዊያን አቆጣጠር ከ2020 ዓም ወዲህ ብቻ 54 ጋዜጠኞች በሙያቸው የተነሳ በደረሰባቸው ጫና አገር ጥለው እንደተሰደዱ ማረጋገጡን ጠቅሷል ፡፡

አሳሳቢው የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት     

ናትናኤል ጌቾ በኢትዮጵያ ዎላይታ ታይምስ የተባለ ድህረ ገጽ መሥራችና አዘጋጅ ነው ፡፡ ናትናኤል በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ተከታዮች ባለው ገጹ ላለፉት ስድስት ዓመታት የደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢን  የተመለከቱ ዘገባዎችን ሲያስተላልፍ ፤  ትችቶችንም ሲያቀርብ ቆይቷል  ፡፡ አሁን ላይ በአካባቢው አስተዳደር  በተደጋጋሚ ተፈጽሞብኛል ባለው እሥርና ወከባ የተነሳ ወደ ኬኒያ መኮብለሉን ይናገራል  ፡፡

ከአገር ለመውጣት የወሰንኩት በድንገት አይደለም የሚለው ጋዜጠኛው “ በተለያዩ ጊዜያት በምሠራቸው ዘገባዎች ከከፍተኛ የመንግሥት ሃላፊዎች ማስፈራሪያዎች እና ዛቻዎች ይደርሱኝ ነበር ፡፡  እስከተወሰነ ጊዜ ትንኮሳዎችን ተቋቁሜ ለመሥራት ሞክሪያለሁ  ፡፡ ነገር ግን ማስፈራሪያዎችን ተከትሎ ለስድስት ወራት ዎላይታ ሶዶ ከተማ ውስጥ ለእሥር ተዳርጊያለሁ ፡፡ በወቅቱ የታሰርኩበት ምክንያት ከአሳሪው አካል ባይገለጸልኝም በቀጥታ ከዘገባዎቹ ጋር የተያያዘ ሥለመሆኑ መገመት ይችላል “ ብሏል ፡፡

ከአዲስ አበባ ለተለያዩ የዓለምአቀፍ የመገናኛ ብዙሃን በግል ዘገባዎችን ሲያቀርብ መቆየቱን የሚናገረው ሌላው ጋዜጠኛ ሄኖክ ተስፋዬ አሁን ላይ በስደት በኬኒያ ናይሮቢ ይገኛል ፡፡ በ2015 ዓም የመንግሥት የፀጥታ አካላት በእኔና በሥራ ባልደረቦቼ ላይ ክትትለ ያደርጉ ነበር ፡፡ ባልደረቦቼ ተይዘው ወደ አዋሽ አርባ መወሰዳቸውን እንደሰማሁ ተመሳሳይ ሁኔታ እንዳይገጥመኝ ወደ ኬኒያ መጣሁ ፡፡ አሁን ላይ የታሰሩት ባልደረቦቼ የተፈቱ ቢሆንም ወደአገር ተመልሶ ለመሥራት ግን ምቹ ሁኔታ ባለመኖሩ ለጊዜው እዚሁ ለመቆየት ተገድጃለሁ “ ብሏል ፡፡

የት ይደርሳል የተባለው የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት

በኬኒያ በስደት ተጠልለው የሚገኙት ናትናኤል አና ሄኖክ በኢትዮጵያ በ2010 የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ በመገናኛ ብዜሃን ነጻነት ላይ ተስፋ ሰጪ ለውጦች መታየት ጀምሮ እንደነበር ያስታውሳሉ ፡፡ በተለይም በእሥር ላይ ይነበሩ ጋዜጠኞች እና ፖለቲከኞች መፈታት ዋነኛ የዴሞክራሲ ማሳያ ተደርጎ በሚቆጠረው የመገናኛ ብዙሃን ነጻነትን ላይ ተስፋን ዘርቶ እንደነበር የጠቀሱት ጋዜጠኞቹ  “ በሂደት ግን በሰሜን ኢትዮጵያ እና በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች የተነሱ ጦርነቶችንና ግጭቶችን ተከትሎ በዘርፉ እና በሙያተኛው ላይ ጫና ማሳደር ተጀመረ ፡፡  እሥር እና ወከባን ጨምሮ በተለያየ መልክና አይነት የሚደረገው ጫና እየተባባሰ መጣ ፡፡ ይህም ቀደምሲል  የነበረውን ተስፋ እንዲሟሽሽ አድርጎታል ፡፡ አሁን ላይ አይደለም በሚዲያ ተቋም እንደ ዜጋ በግለሰብ ደረጃ ሀሳብን መግለጽ አሥፈሪ ሆኗል “ ብለዋል ፡፡

የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውትወታ  

በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት እና በጋዜጠኞች ላይ እየደረሰ ይገኛል በተባለው ወከባ እንዳሳሰባቸው የተለያዩ ዓለምአቀፍ ድርጅቶች በተደጋጋሚ በሚያወጧቸው ሪፖርቶችን እየገለጹ ይገኛሉ ፡፡ በተለይም ሲ-ፒ-ጄ የተባለው ዓለምአቀፍ የጋዜጠኞች መብት ተቆርቋሪ ድርጅት “ በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን  ነጻነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠበበ መጥቷል “ ሲል አስታውቋል ፡፡ “ እኛ እንደ ሲ-ፒ-ጄ  ባለፉት ጥቂት ዓመታት በኢትዮጵያ የተመለከትነው በፕሬስ ነጻነት ላይ የሚደርሰው ጫና እየበረታ መምጣቱን ነው “ በማለት የጠቀሱት በድርጅቱ የምሥራቅ አፍሪካ ቢሮ አስተባባሪ ሙቶኪ ሙሞ “ ጋዜጠኞች ደህንነታቸው ወደ ተጠበቁ አካባቢዎች የሚያደርጓቸው ሽሽቶች ጨምረዋል ፡፡  በቅርቡ ባደረግነው የዳሰሳ ጥናት ከ2020 ዓም ወዲህ ብቻ 54 ጋዜጠኞች በሙያቸው ምክንያት በደረሰባቸው ጫና አገር ጥለው መሰደዳቸውን አረጋግጠናል  ›› ብለዋል ፡፡

የመንግሥት ምላሽ እና የሲ-ፒ-ጄ ምክረ ሀሳብ

የመገናኛ ብዙሃን ነጻነትን ይደፈጥጣል በሚል ተደጋጋሚ ትችቶች እየቀረበበት የሚገኘው የኢትዮጵያ መንግሥት የድርጅቶቹን ወቀሳ አይቀበለም ፡፡ ይልቁንም እንዳንድ ጋዜጠኞቹ ፅንፈኛ ሲል ከሚጠራቸው ታጣቂ ቡድኖች ጋር ግንኙነት አላቸው ፣ ግጭት ቀስቃሽ እና የአገሪቱን ህገ መንግስት የሚጻረሩ ዘገባዎችን ያሰራጫሉ ሲል ይከሳል ፡፡ የጋዜጠኞች መብት ተቆርቋሪው ሲ ፒ ጄ የናይሮቢ ቢሮ አስተባባሪዋ ሙቶኪ ሙሞ ግን ድርጅታቸው መፍትሄ ያለውን ምክረ ሀሳብ ለመንግሥት መጠቆሙን ገልጸዋል ፡፡

አሁንም ከአንዳንዶቹ ጋዜጠኞች ደህንነት እንደማይሰማቸውና በሥጋት ውስጥ እንደሚገኙ ሪፖርት እየደረሳቸው እንደሚገኝ የጠቀሱት አስተባባሪዋ “  ይህም ባልተቋረጠ ፍርሃት ውስጥ እንዳሉና መደበኛ ሥራቸውም ሆነ ኑሯቸው በተጽኖ ሥር እንደሚገኝ ያሳያል  ፡፡ ዋናው ነገር መፍትሄው ምን ይሁን የሚለው ነው  ፡፡ መፍትሄው ለስደቱ መነሻ የሆነውን ነገር ማስተካከል ነው ፡፡ ያ ማለት በቀላሉ ጋዜጠኞች ሳይሰደዱ በአገራቸው ተረጋግተው የሚሠሩበትን ከባቢ ማመቻቸት ይገባል  ›› ብለዋል ፡፡