የመቐለ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ መድህን ሓጎስ በ76 ዓመታቸው ወንድ ልጅ የመታቀፋቸው ጉዳይ አነጋጋሪ ሆኗል።

” ፈጣሪ ምን ይሳነዋል ? የማይገመተው በሱ ፍቃድ ሆኗል። በወጣትነቴ ያጣሁትን የልጅ ጥማት በእርጅና ጊዜ መልሶልኛል ፈጣሪ ይመስገን ! ልጄን የማሳድግበት ጤና ይስጠኝ እድሜ ይጨምርልኝ ” – በ76 ዓመታቸው ወንድ ልጅ የወለዱት ወ/ሮ መድህን ሓጎስ

የመቐለ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ መድህን ሓጎስ በ76 ዓመታቸው ወንድ ልጅ የመታቀፋቸው ጉዳይ አነጋጋሪ ሆኗል።

የድምፂ ወያነ ቴሌቪዥን በእናቲቱ መኖሪያ የተዘጋጀውን የክርስትና ድግስ ላይ ተገኝቶ ያጠናቀረውን ፕሮግራም ከትላንት ጀምሮ በሰፊው ህዝብ ጋር ሲዳረስ ነበር።

እናቲቱ በ76 ዓመታቸው መውለዳቸው በዓለም የድንቃድንቅ መዝገብ ላይ እንዲሰፍር ያለመ የ ‘ X ‘ ዘመቻም አለ።

የማህበራዊ ትስስር ገፅ ተጠቃሚዎች ” እናቲቱ በተለመደው ተፈጥሯዊ መንገድ ነው የውለዱት ” ፤ ” የለም በህክምና ቴክኖሎጂ በመታገዝ ነው ልጃቸውን የታቀፉት ” የሚሉ ክርክሮች በማንሳት ሲፅፉ ታይተዋል።

እናቲቱ በድምፂ ወያነ ቴሌቪዥን እና ሰግለለት ለተባለ ዩቱብ በሰጡት ቃለ-መጠይቅ የተከራካሪዎቹን ጥያቄ ያልመለሰ ድፍን ያለ እንደሆነ የቲክቫህ ኢትዮጵያ የመቐለ ቤተሰብ አባል ገልጿል።

የመቐለው አባላችን ፤ እናቲቱ በትግርኛ ቋንቋ ለሚድያዎች የሰጡት ቃለ-መጠይቅ እና የማህበራዊ የትስስር ገፅ ተጠቃሚዎች ያገኘውን መረጃ ከታማኝ የመረጃ ምንጭ ጋር ለማቀናጀት ጥረት አድርጓል።

ወ/ሮ መድህን ሓጎስ ከዚህ በፊት ልጅ  እንዳልወለዱ ፤ የአሁኑ የመጀመሪያ ልጃቸው መሆኑን በልጃቸው ክርስትና ቀን በአንደበታቸው አረጋግጠዋል። 

ወ/ሮ መድህን በሰጡት ቃለ-መጠይቅ ፅንሳቸውን እስከ 8 ወር ድረስ ደብቀውት እንደነበር ከመግለፅ ባለፈ በተለመደው መንገድ ነው የወለዱት ወይስ በህክምና የታገዘ የስነ ተዋልዶ ዘዴ (IVF or In Vitro Fertilization) ጥበብ ያሉት ነገር የለም።

የቲክቫህ ኢትዮጵያ የመቐለ ቤተሰብ አባል ከታማኝ ምንጭ ባገኘው መረጃ እናቲቱ የወለዱት በኢንቪትሮ ፈርትላይዜሽን (IVF) ማለትም የወንዱ ዘር እና የሴቷን እንቁላል አውጥቶ ከማህፀን ውጪ በላብራቶሪ ውስጥ እንዲዋሃዱ የሚደረግበት በህክምና የታገዘ የስነ ተዋልዶ ዘዴ መሆኑን ተረድቷል።

ወ/ሮ መድሂን ህክምናውን ለማግኘት ወደ ታይላንድ ተጉዘዋል።

በዚያው ፅንሱ የ3 ወር ዕድሜ እስኪ ሞላው ድረስ ቆይተዋል።

ከሦስተኛው እስከ ወሊድ ባሉት ጊዜያት የፅንስ ክትትል በመቐለ በሚገኝ አንድ የግል ህክምና ተከታትለው በቀዶ ህክምና ለመውለድ መቻላቸውን ቲክቫህ ኢትዮጵያ አረጋግጧል።

በኢትዮጵያ የወሊድ ህክምና በህግ የተፈቀደው IVF / In Vitro Fertilization የህክምና ጥበብ በመቐለ ጨምሮ በአዲስ አበባ እንደሚሰጥ እየታወቀ እናቲቱ ለምን ውጭ ድረስ ለመጓዝ እንደፈለጉ የታወቀ ነገር የለም።

በ76 ዓመታቸው ነው ልጅ ለማቀፍ የቻሉት ወ/ሮ መድህን ሓጎስ እሳቸውም ልጃቸውም በመልካም የጤና ሁኔታ ላይ ይገኛሉ።

” ፈጣሪ ምን ይሳነዋል ? የማይገመተው በሱ ፍቃድ ሆኗል። በወጣትነቴ ያጣሁትን የልጅ ጥማት ፤ በእርጅና ጊዜ መልሶልኛል ፈጣሪ ይመስገን። ልጄን የማሳድግበት ጤና ይስጠኝ እድሜ ይጨምርልኝ ” ብለዋል።

ከዚህ ቀደም እ.ኤ.አ. በመስረከም 7/2019 የህንድዋ አንድህራ ፕራደሽ ግዛት ተወላጅ የሆኑት ወ/ሮ ማንጋያማ ያራማቲ በ73 ዓመታቸው በIVF ልጅ በማግኘት በእድሜ ትልቋ ተብለው ነበር።

ባለፈው ዓመት ሳፊና ናሙኩዋያ የተባሉ ኡጋንዳዊ ሴት በIVF ህክምና የመንትያ ልጆች እናት መሆን እንደቻሉ በስፋት ተዘግቦ ነበር።

እንደ አንድ የጤና መረጃ አሜሪካ ውስጥ ከሚወለዱት ህጻናት 2% የሚሆኑት በIVF, or  In Vitro Fertilization የህክምና መንገድ ሲሆን ከ8 ሚሊዮን በላይ ህፃናት በዚህ መንገድ ተወልደዋል።

NB. ኢንቪትሮ ፈርትላይዜሽን (IVF) ማለት የወንዱ ዘር እና የሴቷን እንቁላል አውጥቶ ከማህፀን ውጪ በላብራቶሪ ውስጥ እንዲዋሃዱ የሚደረግበት በህክምና የታገዘ የስነ ተዋልዶ ዘዴ ነው። በላብራቶሪ ውስጥ የተፈጠረው ፅንስ በሚፈለገው ደረጃ እድገቱን ከቀጠለ በኋላ ወደ ሴቷዋ ማህፀን በማስገባት የተፈጥሮ እርግዝና ሂደቱን እንዲቀጥል የሚደረግ ይሆናል፡፡