የአውሮፓ ኅብረት የአስቸኳይ አደጋዎች መከላከያ ቢሮ፣ በአማራ ክልል እንደገና ባገረሸው የኮሌራ በሽታ የሦስት ሰዎች ሕይወት መጥፋቱን ዛሬ ባሠራጨው መረጃ አስታውቋል።
ቢሮው፣ በምዕራብ ጎንደር ዞን 122 ሰዎች በበሽታው እንደተያዙና በቋራ እና በገንዳ ውሃ ወረዳዎች ብቻ ኹለት ሰዎች በበሽታው እንደሞቱ ማረጋገጡን ገልጧል።
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ደሞ አንድ ሰው በበሽታው እንደሞተና በባሕርዳር ከተማ 33 ሰዎች በበሽታው እንደተያዙም የቢሮው መረጃ አመልክቷል።
የበሽታው መነሻ፣ ቋራ ወረዳ ውስጥ የሚገኝ በርሜል ጊዮርጊስ የሚባል የጸበል ቦታ እንደኾነ የጠቀሰው ቢሮው፣ ጸበሉን ለመጠቀም ከሌሎች የክልሉ አካባቢዎች በርካታ ሰዎች ስለሚሄዱ በሽታው የመስፋፋት ዕድሉ ከፍተኛ ነው ብሏል።
በክልሉ የሚካሄደው ግጭት ለረድኤት ድርጅቶች እንቅስቃሴ እክል እንደሆነ መቀጠሉንም ማዕከሉ ገልጧል።